ለ22 ፕሮጀክቶች 26 እስታንድባይ ጀኔሬተሮች /standbygenerators/ የግዥ የውል ስምምነት ተፈረመ።
ህዳር 24/2018 ዓ/ም (ውኢሚ) የውሃና ኢኘርጂ ሚኔስቴር በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት ለሚገነቡ እና ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ 22 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች 26 እስታንድባይ ጀኔሬተሮች /stand bygenerators/ ጨረታውን ካሸኘፈው ሲራም ትሬድንግ ኃ.የተ.የግል ማህበር ጋር 183,116,851.75 ብር የግዥ የውል ስምምነት ተፈርሟል።
የውል ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚንስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት የሚገነቡ በአጠቃላይ በ55 ወረዳዎች 110 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልፀው ጀኔሬተሮቹ የሚገዛላቸው 22ቱ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙና በመጠናቀቅ ላይ የሉ ናቸው ብለዋል።
ክቡር ሚንስትር ድኤታው የጄኔሬተሮቹ ግዢ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልፁ አካባቢዎቹ ውሃ አጠር መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት ፕሮጀክቶቹ በቂ፣ዘላቂና የማይቆራረጥ አገልግሎት ለህብረተሰቡ እንዲሰጡ ታስቦ ነው ብለዋል።
ዶ/ር አምባሳደር አክለው የግዢውን ጨረታ ያሸነፈው ድርጅት ከዚህ ቀደም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ አቅርቦቶችን በግዢ የማቅረብ ጥሩ ልምድ እንደነበረው ጠቅሰው አሁንም ደረጃውን የጠበቀ ዕቃ በፍጥነት በማቅረብ የውሃ ችግር እንዲፈታ የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።
በመጨረሻም ለግዢው ሂደት መፋጠን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ባለሙያዎች በሚያስፈልግ ሁሉ ከጎናችሁ ነን ብለዋል።
የሲራም ትሬድንግ ኃ.የተ.የግል ማህበር ዋና ስራስኪያጅ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ካሳየነው ብቃት በተሻለ መልኩ በፍጥነት ደረጃቸውን የጠበቁ ጄኔሬተሮችን እናቀርባለን ብለዋል።