በክትትልና ግምገማ እና የመማማር ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ።
በክትትልና ግምገማ እና የመማማር ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ።
ህዳር 13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በክትትልና ግምገማ እና የመማማር ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ።
የውይይት መድረኩን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በፕሮጀክቶች ሳይት ዙሪያ ድጋፍና ክትትል በሚደረግበት ወቅት ኮንትራክተሮች ምን እንደሚሰሩ በጥልቀት መመርመር፣ አማካሪዎች ሚናቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን መቃኘትና የመስሪያ ቤቱን አቅርቦት መፈተሽ ይገባል ያሉ ሲሆን እስከ ነሀሴ ወር መጨረሻ እያንዳንዱ ፕሮጀክት ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም ረቂቅ ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ከዘልማድ አሰራር መላቀቅ፣ በቅንጅትና በመናበብ መስራት እና ተፅዕኖዎችን መለካት ያስፈልጋል ብለዋል።
በጨማሪም የተቋሙን መረጃ በማዘመን የሚከናወኑ ተግባራትም 70 በመቶ መድረስ አለበት ሲሉም በአፅንዖት አሳስበዋል።
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ የውይይቱን አላማ አስመልክቶ እንደተናገሩት በቀጣይ አምስት ዓመታት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚከናወኑ ዕቅድ ዝግጅት፣ አተገባበር እና ሪፖርት አቀራረብ ወቅት ግልፅነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ የሚፈፀሙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት ማድረግና ወደ ተግባር መግባት በማስፈለጉ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ኦልቀባ አክለውም በሚኒስቴሩ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞችን በማስማማት ተቋማዊ የማድረግ፣ የማስተዋወቅና የተገኙ ውጤቶችን በማደራጀትና በማሰራጨት ወጥነት ያለው ስራ መስራት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የክትትልና ግምገማ እና የመማማር ማዕቀፍ የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር አድማሱ ቴሶ ሲሆኑ በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችን በግብዓትነት ሰንዝረው በቀጣይ ለአመራሩ፣ ለማኔጅመንት አባላትና በሌሎች ባለሙያዎች አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በፕሮጀክቶች ዙሪያ በሚካሄድ የክትትልና ድጋፍ ስራ ላይ በዋናነት የተቋራጩ ግልፅና ጥራት ያለው ዕቅድ፣ አመላካቾች፣ ተፅዕኖዎች እና ስጋቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም በመድረኩ ተጠቅሷል።
በውይይት መድረኩ ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ እና እስከ ቡድን መሪ ድረስ ያሉ አመራሮች ተሳትፈዋል።