63ኛው የአፍሪካ ቀን ተከበረ።

63ኛው የአፍሪካ ቀን ተከበረ።

ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጁትና "የአፍሪካ ቀን 2026"ን የሚዘክርና 63ኛውን የአፍሪካ ቀን እየተካሄደ ይገኛል።

ኮንፈረንሱ “የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና አስተማማኝ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ” /"Assuring Sustainable Water Availability and Safe Sanitation Systems to Achieve the Goals of Agenda 2063"/ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የውሃ ደህንነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ኮንፈረንሱ 63ኛው የአፍሪካ ቀን በአፍሪካ የውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማትን ለማሻሻል የሚያስፈልገውን አስቸኳይ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ትኩረት ያደረገም ነበር።

የውሃ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓት፣ የማህበረሰብ የመቋቋም አቅም፣ ሳይንስና ኢኖቬሽን፣ ፓን-አፍሪካኒዝም እና አንድነት፣ እንዲሁም ዘላቂ መፃኢ እድል በሚሉ ስድስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገ ነው።

በመድረኩ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የውሃ ደህንነትና አረንጓዴ ኢነርጂ ፍላጎትን ከማሳካት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ የኃይል አቅርቦትና ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር እንደ ትልቅ ስኬትም ቀርቦ፤ ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትንም ተሞክሮ አጋርታለች።

የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በጋራ በማስተባበር ረገድ ውጤታማ የሆነው "የተቀናጀ የውሃ፣ የንፅህና እና የጤና አጠባበቅ (One WASH National Program)" ተሞክሮም ለተሳታፊዎች ቀርቧል።

ለፈጣን የከተሞች ዕድገትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ክፍተቶችን በአጋርነት ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችም በመድረኩ ተመላክቷል።

ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አለምአቀፍ ሚዲያዎች፣ አካዳሚክና ፕሮፌሽናል ምሁራኖች በመድረኩ ተሳታፊ ናቸው።

Share this Post