174 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ኃይል ፕሮጀክት በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለፀ።

174 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ኃይል ፕሮጀክት በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለፀ።

ሚያዝያ 07/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የተመራ ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ኬና ወረዳ ጌራ ቀበሌ ከGIZ እና ከክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር እያስገነባው የሚገኘውን የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጎበኙ።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በመተግበር እ.ኤ.አ በ2030 ህብረተሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀው፤ የሶላር ሀይል ፕሮጀክቱ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን ውጤቶች በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ፕሮጀክት እንደሆን ገልፀዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ይህ ዘርፈ ብዙ የሆነው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ1 ሺ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ መሰል ቴክኖሎጂዎችን ከማስፋፋት አንፃር ፕሮጀክቱ ህብረተሰቡን ኃይል ተጠቃሚ ከማድረግ አልፎ ማስተማሪያም በመሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ በአግባቡ እንዲንከባከብ አሳስበዋል።

የኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ዋና አስተዳደሪ አቶ ገልገሎ ገልሾ ለቡድኑ አቀባበል ካደረጉ በኋላ በሰጡት አስተያየት ለወጣቱ የስራ ዕድል የሚፈጥር ፕሮጀክት በመሆኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የእድሉ ተጠቃሚ እንድንሆን ስላደረገን እናመሰግናለን ብለዋል።

በGIZ ፕሮጀክት የማህበረሰብ ልማት አማካሪ አቶ ተስፋዬ ዳና በበኩላቸው የሶላር ቴክኖሎጂው ከአምስት አመት በፊት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረ መሆኑን አውስተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በሶስት ክልሎች በአምስት ቀበሌ ላይ የሚሰራው ይህ ፕሮጀክት በጌራ ቀበሌ በ100 ሚሊየን ብር ወጪ ተገንብቶ 174 ኪሎ ዋት እንደሚያመነጭና በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ በጉብኝቱ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት እንዲህ አይነት ብዙ ገንዘብ የሚፈልግ የሀይል ፕሮጀክት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን አቅዶ በመስራት የመጀመሪያው ቢሆንም፤ ክልሉ አዲስ መዋቅር ላይ ስለነበር በበጀት እጥረት ምክንያት የነበሩ ክፍተቶችን በመፍታት በቀሩት ወራት ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

በመጨረሻም የጌራ ቀበሌ ተወላጅ እና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር የሆኑት በላቸው ቦረንቶ በበኩላቸው እንደተማሪ ከዚህ ቀበሌ ያለ መብራት እስከዩኒቨርስቲ መጓዛቸውን ገልጸው፤ ከዚህ ፕሮጀክት መሳካት በኋላ ያለው ትውልድ በሀገሪቱ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ማገልገል የሚችሉ ተማሪዎች ስለሚወጡ ዕድለኞች ናቸው ብለዋል።

Share this Post