16th East African Power pool የሚኒስትሮች ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡

16ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር (East African Power pool) የሚኒስትሮች ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡ በካምፓላ ኡጋንዳ ፌብሩዋሪ 03/ 2023 የተካሄደው 16ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር (East African Power pool) የሚኒስትሮች ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡ የሃይል ትስስሩ የ13 አባል ሀገራት የኤሌክትሪክ ኩባንያዎች ዋና ሥ/ አስፈጻሚዎች፤ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና የልማት አጋሮች ለተከታታይ ሁለት ቀናት ተሰብስበው ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ለውሳኔ መብቃቱ ተገልጿል። በመጀመሪያ ደረጃ ለውሳኔ የቀረበው የሃይል ትስስር ተቋሙን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ታንዛኒያዊው ጄነራል ሴክሬታሪ ኢ/ር ለቢ ቻንጉላ በአዲስ እንዲተኩ የቀረቡትን ዕጩ አይቶ ማፅደቅ ሲሆን፤ በውድድር ከኬንያ አሸናፊ የሆኑትን የኢ/ር ጀምስ ካራሪ ዋሆጎን የጀነራል ሴክሬታሪነት ምርጫ አጽድቋል። በመቀጠል ለውሳኔ የቀረበው በገለልተኝነት የሃይል ትስስር ተቋሙን የሚቆጣጠረው የሬጉላቶሪ ቦርድ መቀመጫ በካምፓላ ኡጋንዳ እንዲሆን ሲሆን ውይይት ተደርጎበት እንዲፀድቅ ተደርጓል። ሌሎቹ ሁለት አጀንዳዎች ማለትም የሁለትሽ የሃይል ሽያጭ ፍሬም ወርክ ስምምነት (EAPP Bilateral Trading Agreement Framework) ጥናትና ከዚህ በፊት በሀገሮች መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት (Intergovernmental MOU) ሰነድ የማሻሻል ሥራ በመጪው ጁን 2023 በሚደረገው አስቸኳይ ስብሰባ አይቶ ለመወሰን ስምምነት ላይ ተደርሷል። በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የተሳተፉ ሲሆን፤ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የተደረገው የሚኒስትሮች ስብሰባና የፀደቁት የውሳኔ ሃሳቦች በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረገውንና እየተደረገ ያለውን የሃይል ትስስር የበለጠ የሚያጠንክር በመሆኑ ሁሉም አገሮች ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም የሀይል ትስስሩን ለማጠናከር የበኩሉዋን ሚና እንደምትወጣ ገልጸዋል።

Share this Post