15ኛው ሀገር አቀፍ የከተሞች የውሃ ፎረም ተካሄደ፡፡

15ኛው ሀገር አቀፍ የከተሞች የውሃ ፎረም ተካሄደ፡፡ ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የከተሞች የመጠጥ ውሃ ፌዴሬሽንና ከአምቦ ጉደር ከተማ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ጋር በጋራ 15ኛውን ሀገር አቀፍ የከተሞች የውሃ ፎረም በአምቦ ከተማ ተካሄደ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር የውሃ አስፈላጊነትን በሚገባ ተረድተን ውሃን ስናስተዳድርና ስንመራ የተሻለ አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል። የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አፈፃፀምን መቶ ለማድረስ እየሰራን ነው ያሉት ክብር ሚንስትሩ የህብረተሰቡን ፍትሃዊ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ውጤታማነት ላይ ልናተኩር ይገባል ብለዋል። የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀጫሉ ገመቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት አምቦ ከተማን ለኑሮና ለነዋሪዎች ምቹ እና ተመራጭ ለማድረግ ከለውጡ ማግስት የውሃ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ተጠቃሚ ለማድረግ ተግተን እየሰራን ነው ብለዋል። ክቡር ከንቲባው አክለውም የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳያጋጥምና የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ንፁህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ፎረሙ "ዘመናዊ የመረጃና የአስተዳደር ስርዓትን መዘርጋት ለዘላቂ የከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው መድረክ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል። በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ አማካሪዎች፣ ክቡር አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ፣ የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ፣የአምቦ ዩንቨርሲቲ አመራሮች፣ የውሃ መሳሪያ አቅራቢዎች፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ከየክልሉ የከተሞች የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊዎችና ተወካዮች እየተሳተፉ ነው፡፡

Share this Post