የውሃ ሂሳብ አከፋፈል ስርዓትን ለማዘመን (Water billing system software) የሚያስችል የውል ስምምነት ተደረገ፡፡
ታህሳስ /2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ15 ከተሞች የውሃ አገልግሎት ተቋማትን የውሃ ሂሳብ አከፋፈል ስርዓትን ለማዘመን ከዳፍቴክ ኮምፒዩተር ኢንጂነሪግ ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ከውሃ ሂሳብ አከፋፈል ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን በመቅረፍ በሲዳማ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች 15 ከተሞች ላይ የውሃ ሂሳብ አከፋፈል ስርዓትን ለማዘመን ሶፍት ዌሮችን ለመጫን የተደረገ ስምምነት መሆኑንና በተመረጡት ከተሞች እስከ 4 ወር ባለው ጊዜ ሲስተሙን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ስራ እንደሚሰራ የዳፍቴክ ኮምፒዩተር ኢንጂነሪግ እምነት እንደተጣለበት ተናግረዋል፡፡
የዳፍቴክ ኮምፒውተር ኢንጅነሪግ ዋና ስራ አስኪጅ አቶ ደነቀው በሪሁን ድርጅቱ ከ13 ዓመት በላይ በዘርፉ ልምድ ያካበተና ከ130 በላይ ከተማዎች የውሃ አገልግሎት ተቋማትን የሲስተሙ ተጠቃሚ ማድረጉንና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልሎትን ጨምሮ ሶፍት ዌሩን ለማስገጠም የገንዘብ አቅም ችግር ላለባቸው 5 ከተሞች በነጻ የአገልሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን ገልጸው፤ ሲስተሙ በዋናነት ከቆጣሪ አንባቢ እና ሂሳብ አከፋፈል ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ትክክለኛው አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም ሶፍትዌሩ በየወሩ በቴክስት በሞባይል አገልግሎት የሚተገበርና በየክልሎቹ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ለቢል አዘጋጅ፣ ለቢል ሻጭ፣ ለቢል አንባቢና ለሀላፊ ስልጠና ተሰጥቶ የሚተገበር መሆኑንና አሁን ላይ ሲስተሙን ውል በተገባነው መሰረት ከ4 ወር ጊዜ ውስጥ በ15ቱም ከተሞች በመግጠም የአገልሎቱ ተጠቃሚ እናደርጋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የውል ስምምነቱ 4.2 ሚሊየን ብር የሚገመት ሲሆን፤ ከጣሊያን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሸፈን ይሆናል፡፡