አገልግሎት ያቋረጡ የውሃ ተቋማት እንዲያገግሙ በማድረግ (Rehabilitation) አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

አገልግሎት ያቋረጡ የውሃ ተቋማት እንዲያገግሙ በማድረግ (Rehabilitation) አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ግንቦት /2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) አገልግሎት ያቋረጡ የውሃ ተቋማት እንዲያገግሙ በማድረግ (Rehabilitation) አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ ። የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ከአስቸኳይ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዴስክ ጋር በቡራዩ ከተማ አገልግሎት ያቋረጡ እና የውሃ ምርት የቀነሱ የውሃ ተቀማት በማጠብና በማደስ አገልግሎት መስጠት የጀመሩና ለመጀመር በሂደት ላይ ያሉ የውሃ አቅርቦት ጉድጓዶችን የመስክ ምልከታ አካሂደዋል። በመስክ ምልከታ ላይ ገለፃ ያደረጉት የአስቸኳይ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዴስክ ኃላፊ ተወካይ አቶ ገቢቴ ገነሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዳዲስ የውሃ ተቋማትን አስገንብቶ ወደ አገልግሎት ከማስገባት በተጨማሪ አገልግሎት ያቋረጡ እና የውሃ ምርት የቀነሱ የውሃ ተቋማት በማጠብና በማደስ አገልግሎት እያስጀመረ ይገኛል ብለዋል። ከዚህ በፊት የውሃ ተቋማት ተገንብተው ወደ አገልግሎት ከገቡ በኋላ ጉድጓዶቹ ውሃ ምርት የቀንሱና ከአገልግሎት ወጭ ሲሆኑ የጉድጓዶቹ ማገገሚያ (Rehabilitation) ስራ ትኩረት ባለመሰጠቱ እና አገልግሎት ውጪ የሚሆኑ የውሃ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ሀገራዊ የውሃ አቅርቦት ሽፋን ላይ ተፅዕኖ እያመጣ ይገኛል ብለዋል፣፡ አቶ ገቢቴ አያይዘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘላቂ የልማት ግቦችን (SDG) ለማሳካት ከሚተገብራቸው አንዱ ህብረተሰቡን በውሃ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው ዘላቂ የውሃ አቅርቦት ለማረጋገጥ አቅም ውስንነት ያለባቸውን የውሃ አገልግሎቶች ለመደገፍ የተቀረጸ ፕሮግራም ነው ብለዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአስቸኳይ መጠጥ ውሃ ዴስክ የጉድጓድ ጠረጋ አስተባባሪ አቶ አበራ ኩማ በበኩላቸው አዳዲስ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ከማከናወን ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ያቋረጡ የውሃ ተቋማት መጥረግ እና ማደስ አስፈላጊ ነው ብለዋል። እንደነዚህ አይነት አገልግሎቱን በክልሎች እና በውሃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ የክልሎችን ጥያቄዎች እና የችግሩ ስፋት በነበረው ሁኔታ መሸፈን ባለመቻሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በልዩ ሁኔታ የውሃ ተቋማት ማደሻ ማሽኖችን አሰማርቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልፀዋል። በነባር የጉድጓድ እድሳት ከወጪና ከጊዜ አንፃር ከአዲሱ ጉድጓድ ከመቆፈር ብዙ እጥፍ ልዩነት በመኖሩ ነባር ጉድጓዶችን አድሶ መጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። የሸገር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የቡራዩ ቅርንጫፍ የውሃ አቅርቦት ጥራት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ተመስገን ሙሉጌታ የቡራዩ ከተማ የውሃ አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት መኖሩን ገልፀው፤ ቀደም ተብለው የተቆፈሩ ጉድጓዶች በየጊዜው ማጠብና ማፅዳት ባለመቻሉ አገልግሎት ያቋረጡ እና ከግማሽ በታች አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ የውሃ ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል ።

Share this Post