የአንድ_ቋት ዋሽ (oneWASH) ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም (MIS) ማሻሻያ የመነሻ ሪፖርት /Inception Report /ወርክሾፕ ተካሄደ።

የአንድ_ቋት ዋሽ (oneWASH) ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም (MIS)ማሻሻያ የመነሻ ሪፖርት /Inception Report /ወርክሾፕ ተካሄደ። ግንቦት 06/2018 ዓ/ም ውኢሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአንድ_ቋት ዋሽ (oneWASH) ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም (MIS) ማሻሻያ የመነሻ ሪፖርት /Inception Report /ወርክሾፕ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጌትፋም ሆቴል አካሂዷል ። የወርክሾፕ መድረኩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ አስተማማኝና ውጤታማ የመረጃ ስርዓት ትክክለኛ ዕቅድ ለማቀድ፣ለውሳኔ አሰጣጥ ፣ክትትል ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማስፈን እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል። የዋን ዋሽ /oneWASH/ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም (MIS) ባለፉት ዓመታት ቅንጅታዊ አሰራርና ሪፖርት አቀራረብን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና የነበረው ሲሆን እያደገ የመጣውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፍላጎት ለማሟላት ፣ለተሻለ የተቋማት ትስስርና ወቅታዊና ተዓማኒ ሪፖርት ለማቅረብ የዘርፉን ሲስተም ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል። የሲስተሙ መሻሻል ዓላማ በሶፍትዌር ላይ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን በባለድርሻ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያጎለብት ፣የመረጃ ጥራትን በማሻሻል ግልጽነትን በማስፈን ፣የፖሊሲና የኢንቨስትመንት ውሳኔዎችን የሚደገፍ ዘመናዊ፣የተቀናጀ፣ቀልጣፋና ለተጠቃሚ ምቹ አሰራርን ለመፍጠር ነውም ብለዋል። የሲስተሙ ስኬት የሚወሰነው በሁሉም የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት በመሆኑ የተሳታፊዎች የቴክኒክ ክህሎት ፣ተቋማዊ ልምድ ፣ገንቢ አስተያየት እንዲያቀርቡ እና መነሻ ሪፖርቱን በጥንቃቄ በመገምገም የስራውን ጥራትና ውጤታማነት የሚያጠናክር ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርቡ አበረታታለሁ ብለዋል። በመጨረሻም አምባሳደር አስፋው የሲስተሙን አማካሪ ድርጅቶች ኤል-ሀደር ኢንጂነሪንግ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር /El-Hadar Engineering PLC/ እና ኢ-ሰርቪስ አፍሪካ ሊሚትድ /eService Africa Ltd./ የጋራ ሽርክና በዘርፉ እስካሁን ላደረጉት ጥረት አመስግነው በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ለዘርፉ ጥራት ያለውን ፣ዘላቂ፣ወሳኝና ጠንካራ መፍትሄ እንደሚያቀርብ እምነቴ ነው ብለዋል። በመድረኩ በጉዳዩ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሰፊ ሀሳብ የያዙ ሰነዶች በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርቦ ተሳታፊዎች ተወያይተው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረክ ማብራሪያ፣ምላሽና የወደፊት የትግበራ አቅጣጫ ተሰጥቷል ። በወርክሾፑ የክልሎች የዋንዋሽ ፕሮጀክት አስተባባሪዎች ፣የሲስተም አማካሪ ድርጅቶች ተወካዮች ፣የተለያዩ አጋር ድርጅቶችና ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ሀላፊዎች ተገኝተዋል ።

Share this Post