ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢነርጂ አቅሟን በስፋት ለማልማት ከግሉ ዘርፍ ጋር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት አላትበኢነርጂ ዘርፍ ልማትና አቅርቦት ከተሰማራው KP Group ከተሰኘው የህንድ ኩባንያ ልዑካን ቡድን ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢነርጂ አቅሟን በስፋት ለማልማት ከግሉ ዘርፍ ጋር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት አላት።   የካቲት /2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢነርጂ አቅሟን በስፋት ለማልማት ከግሉ ዘርፍ ጋር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገለጹ።   ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በኢነርጂ ዘርፍ ልማትና አቅርቦት ከተሰማራው KP Group ከተሰኘው የህንድ ኩባንያ ልዑካን ቡድን ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡   በውይይቱ ወቅት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስረዱት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተልዕኮውን ለማሳካት በሶስት ዘርፎች ተደራጅቶ በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ በርካታ መሰረታዊ ስራዎች እየተከናወኑ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡   ኢትዮጵያ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ምስራቅ አፍሪካን ተሻግሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ከዚያም የሚያልፍ የተሳሰረ የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማስፋት ራዕይ ሰንቃ እየሰራች መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። 150 ጊጋዋት የሚገመት የታዳሽ ሀይል አቅም ያላት ኢትዮጵያ 9 ጊጋዋት ብቻ ማልማቷን ገልጸው፤ ታዳሽ ሀይልን ለማልማት የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል፡፡   በኢነርጂ ልማት ዘርፉ የግሉ ዘርፍ ለመጋበዝ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ አስገንዝበው፤ ኢትዮጵያ 98 በመቶ አረንጓዴ ሀይል ባለቤት መሆኗን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ የፀሐይ ሀይል፣ የንፋስ ሀይል፣ ጂኦተርማል፣ የውሀ ሀይልና በጣም አስፈላጊው ግሪን ሃይድሮጂን እምቅ አቅም እንዳላትም ገልፀዋል፡፡   በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የገጽ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ያላት በመሆኗ አረንጓዴ ሃይድሮጂን ለማመንጨትና ለማምረት ለኢንቨስትመንት በጣም ተስማሚ ሀገር ናት ብለዋል፡ በአረንጓዴ ኢነርጂ መሰረተ ልማት እና አገልግሎት ላይ የሚሰራው የህንዱ KP Group ግዙፍ ኩባንያ ልዑካን ቡድን በበኩላቸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና ሰፊ ገለፃ አመስግነዋል። ኩባንያው በቀጣይ አዋጭ በሆነው የኢነርጂ ዘርፍ በኢትዮጲያ ለመሠማራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

Share this Post