በHuman Capital Project (HCP) አዘጋጅነት የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ ተካሄደ።
በHuman Capital Project (HCP) አዘጋጅነት
የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው።
አዳማ፣ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚተገበረው የHuman Capital Project(HCP) ለፕሮጀክቱ ትግበራ እገዛ በሚያደርጉ ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ የስልጠና መርሐ ግብር በአዳማ ከተማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል እየተካሄደ ነው።
መድረኩን የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የHuman Capital Operation ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ዱጉማ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በቁጥር መቶ በሚደርሱ የዓለም ሃገራት የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ከ2016ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የተገባበትና የአምስት ዓመት ቆይታ ኖሮት በ2020ዓ.ም የሚጠናቅ በመሆኑ የሰው ልማትን ለማጠናከር፣የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ጥራት ለማሻሻል እንዲሁም የመንግስት ተቋማት አቅምን ለመገንባትም ጉልህ ሚና የሚጫወት ነውም ተብሏል።
በሃገሪቱ አዲስ አበባ ከተማን ሳያካትት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 65 ወረዳዎች ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኘው ይህ ብሄራዊ ፕሮግራም በመንግስትና በዓለም ባንክ ትብብር የሚተገበር ሲሆን በተለይም በውሃና ሳኒቴሽን፣በጤና ዘርፍ፣በትምህርት ተቋማት እንዲሁም በኢነርጂ ዘርፎች የተሳለጠ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኑሮ ደረጃውን በማሻሻል ችግር ፈቺ ስራ የሚሰራ መሆኑ ተመልክቷል።
በፕሮጀክቱ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ፣ከአጎራባች ሃገራት ከስደት ተመልሰው በመጠለያዎች ለሚኖሩ ዜጎች እና በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ለተደቀኑ ችግሮች ጊዜያዊና ዘለቄታዊ መፍትሄ በመስጠት በርካታ ስራዎች ሲተገበሩ መቆየታቸውንና በአብዛኛው የመቀንጨር (stunting) አዝማሚያ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በጥናት ተለይተው በአካባቢው የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሳደግና የመማር ማስተማር ውጤትን ለማሻሻልም ሰፊ ስራ ተሰርቷል ተብሏል።
እንዲሁም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን የመብራትና የሶላር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድም የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መኖራቸው ተብራርቷል።
ፕሮጀክቱ ከጤና፣ከትምህርት ፣ከግብርና ፣ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበር ሲሆን ይህ ጉዳይም ልዩ ያደርገዋል ሲሉ አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ አለሙ መንገሻ መርሐ ግብሩ በውሃ ፣በግልና አካባቢ ንጽህና (WASH) ፕሮግራሞች ውስጥ ውጤት ተኮር ክትትልና ግምገማን ለማጠናከር ፣የመረጃ ጥራትን ለማሻሻልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አስተዳደር ስርዓትን ለማጎልበት አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ የተቀናጀ ዕቅድ፣በጥራት የተዘጋጀ መረጃ፣ጠንካራ ክትትልና ግምገማና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ ወሳኝ ሚና ስለሚጫወት በዚህ ዙሪያ ከአቅም ግንባታ ስልጠናው ትልቅ ውጤት ይጠበቃል ሲሉ አቶ አለሙ አመልክተዋል።
መርሃ ግብሩ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ቆይታ የሚኖረው ሲሆን በፕሮጀክት ዕቅድና አስተዳደር፣ ግምገማና ክትትል፣በመረጃ አስተዳደር ሂደቶችና ጥራት ማረጋገጫ፣እንዲሁም በpower BI ሶፍትዌር እና የkobo toolbox የመረጃ ማሠባሰቢያ መሣሪያ ላይ ትኩረት አድርጎ ለተሳታፊዎች እየተላለፈ ነው።
በስልጠናው ላይ የተሳተፉት በሲዳማ ክልል ውሃ ፣ማዕድንና ኢነርጅ ቢሮ የዕቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ሐንቄ ፕሮጀክቱ በክልሉ ወደ ስራ ገብቶ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በቀጣይም ከዕቅድ እስከ ግምገማ ለሚኖሩ ተግባራት በርካታ ግብዓት እንዳገኙ አመልክተው ሁሉም ተሳታፊዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ሚካኤል መሃሪ ፣ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ስራ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች የክልል የዕቅድና በጀት የዳይሬክተሮች እንዲሁም የዋን ዋሽ ስፔሻሊስቶች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።