በሶስተኛው ምዕራፍ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ሀይጅን ተደራሽነት ፕሮጀክት (Ethiopian sustainable WaSH Access project Phase III) ላይ ውይይት ተደረገ፡፡
መጋቢት 24/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሶስተኛውን የ“Ethiopian Sustainable WaSH Access Project Phase III” ወደ ተግባር ለማገባት የሚያስችል ውይይት ከዓለም ባንክና ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር አካሄደ።
ውይይቱ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ መሪነት የተካሄደ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በቀጣይ አምስት ዓመታት በገጠርና በከተማ፣ በትምህርትና በጤና ተቋማት፣ እንዲሁም በድንበር አካባቢ የሚገኙ ስደተኞች ላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን ተደራሽነትን ለማሳደግ እንዲያገለግል የታቀደ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ወቅት ዓለም ባንክ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ዕቅድ ያቀረበ ሲሆን፤ እንደተገለፀውም 200 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ፣ 15 በመቶ የመንግስት የማቺንግ ፈንድና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የሚገኝ ድጋፍን በመደመር በአጠቃላይ 460 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንዲመደብ ታቅዷል።
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በንግግራቸው ፕሮጀክቱ እንዲሳካ በተለይ ከአቅም ግንባታ፣ ከበጀት፣ ከደህንነት (Security) እና ከጊዜ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ በጥልቀት እንዲታዩ በአጵንኦት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብይ ግርማ ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለማስባት የሚያስችል ውይይት መካሄዱን በመግለጽ፣ ከቀረበው ዕቅድ ጋር የተያያዙ ማሻሻያዎች በቀጣይ አስር ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደማከናወኑ አመላክተዋል።
ፕሮግራሙ በ103 የገጠር ወረዳዎች፣ በ18 አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች እና በ8 የድርቅ ተጋላጭ ወረዳዎች ላይ እንዲተገበር የታቀደ ሲሆን፣ በተለይም በድንበር አካባቢ ያሉ ስደተኞችን በማካተት ከሁለተኛው ምዕራፍ የተለየ አቅጣጫ እንዳለው ተገልጿል።
ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ይህ ፕሮግራም ውጤትን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ የመጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደግ የተጠቃሚነት ደረጃን እንደሚያሻሽል ተጠቁሟል።
በአጠቃላይ በውይይቱ ወቅት ችግሮች፣ ቅድሚያ የሚሰጡ ጉዳዮች፣ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ስራዎች እና አዳዲስ እቅዶች በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል።