ኢትየጵያ የኃይል ልማት ፍኖተ ካርታዋን (Ethiopia National Energy Compact) በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ አቀረበች - የካቲት 26/2018 ዓ/ም
ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ በዓለም ባንክ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ በጋራ አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ 300 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የኤሌክትሪፊኬሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያልመው ጉባኤ (Mission 300) ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
በጉባኤው የዘርፉ እና የፋይናንስ ሚኒስትሮች፣ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድረሻዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር የተከበሩ ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ በጉባኤው የከሰዓት በኋላ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን የኃይል ልማት ፍኖተ ካርታ (Ethiopian National Energy Compact) አቅርበዋል፡፡
የፍኖተ ካርታው የኤሌክትሪክ እና የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን፣ ብርቱ የኃይል መሰረተ ልማትን ማጠናከር፣ ቀጣናዊ የኃይል ሽያጭ የገበያ ድርሻን ማሳደግ፣ የዘርፉን ተቋማት አቅም ማሳደግ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ የሚሉ አምስት ዋና ዋና አምዶች እንዳሉት አብራርተዋል።
መንግሥት ለዜጎች ተደራሽ የሚሆን የኤሌክትሪፊኬሽን አገልገሎትን ዕውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በምስራቅ አፍሪካ በኃይል ማመንጨት እና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ያላትን ጉልህና ቀዳሚ ሚና ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡
ፍኖተ ካርታው እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ አሁን ያለውን የኤሌክትሪፊኬሽን ሽፋን ተጨማሪ 50 ሚሊዮን ህዝቦችን ተጠቃሚ በማድረግ ወደ 75 በመቶ ከፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ አቅርቦትን ደግሞ ወደ 58 በመቶ ማሳደግ የፍኖተ ካርታው ትኩረት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የምታመርተው ኤሌክትሪክሲቲ 100 በመቶ ከታዳሽ የኃይል ምንጭ እንደሆነ ለመድረኩ የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ እ.ኤ.አ እስከ 2030 አጠቃላይ አገሪቱ የማምረት አቅሟን ወደ 14 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ክቡር ሚኒስትሩ፤ የልማት አጋሮች እና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው፤ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።