የአፍሪካ የኢኮሶክ ምክር ቤት /ECOSOCC-Economic Social & Cultural Council/ዓመታዊ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

የአፍሪካ የኢኮሶክ ምክር ቤት /ECOSOCC-Economic Social & Cultural Council/ዓመታዊ ስብሰባ እየተካሄደ ነው። አዲስ አባባ # የካቲት 02/2018 ዓ.ም ውኢሚ በየዓመቱ ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ስብሰባ ቀደም ብሎ የሚደረግ የአፍሪካ የኢኮሶክ ምክር ቤት /ECOSOCC-Economic Social & Cultural Council/ ዓመታዊ ስብሰባ በስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ ነው።   ECOSOCC የሲቪል ሶሳይቲ ቡድን በየዓመቱ ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ስብሰባ ቀደም ብሎ የሚደረው የምክር ቤቱ መወያያ አጀንዳና መሪ ቃል "ቀጣይነት ያለው የውሃ አቅርቦትንና ምቹ የሳኒቴሽን ሲስተምን ለ2063 አጀንዳ ግብ ማረጋገጥና ማሳካት"/"Assuring Sustainable Water Avilability and Safe Sanitation System to Achive the Goals of Agenda 2063" የሚል መሆኑ ተገልጿል።   የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በመድረኩ ተገኝተው በመወያያ አጀንደ ዙሪያና በአጠቃላይ እንደሀገር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያሳካችውን ስኬቶች፣ በመጡ ለውጦችና በአፍሪካ ደረጃ እንዴት ተቀናጅተን በህብረትና በትብብር መስራት አለብን በሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ንግግር አድርገዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለነዋሪዎች ጽዱ፣ ምቹና ማራኪ አካባቢን ከመፍጠር አንጻር የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስአበባን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች የኮሪደር ልማትን በማካሄድ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል ክቡር ሚኒስትሩ። አፍሪካ ዕምቅና ከፍተኛ የውሃ ሀብት ቢኖራትም ዜጎቿ እስካሁን መጠቀም የሚገባቸውን አለመጠቀማቸው የሚቆጭና አሳዛኝ ጉዳይ መሆኑንም ኢትዮጵያንና ሌሎችንም የአፍሪካ ሀገራትን ለአብነት አንስተዋል። ይህ እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው የአፍሪካ ህዝብ የውሃም ይሁን ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት በትብብር፣ በቅንጅትና በፍትሃዊነት ባለመጠቀሙ በበሽታ፣ በውሃ እጦት፣ በድህነት፣ በድርቅ፣ በረሀብ እና በኋላቀርነት እየማቀቀ ስለሚገኝ አሁን በትብብርና በቅንጅት በመስራት ከዚህ ሁሉ ችግር ለመውጣት ወሳኝ ጊዜ ላይ ደሰናል ብለዋል።   ዶ/ር ሀብታሙ በንግግራቸው የሲቪል ሶሳይቲ ቡድንም ይሁን በአፍሪካ ህብረት መሪዎች ስብሰባ ላይ የውሃና የሳኒቴሽን ጉዳይ መወያያ አጀንዳ መሆኑ መልካም አጋጣሚና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ለስኬቱ ሁላችንም ተኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል። ይህ ቡድን ድምፃቸው ለማይሰማ ድምፅ፣ ለአፍሪካ ልጆች ተስፋ፣ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለሚሄድ የህዝብ ብዛት ሁለንተናዊ መፍትሔ የሚያመቻች እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።   ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በፍትሀዊነት ለመጠቀም፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አካባቢን ለመፍጠር የቡድኑ መጠናከር ወሳኝነት አለው ብለዋል። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ አነሳሽነት ተጀምሮ የተሳከው በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 48 ቢልዮን ችግኞችን መትከል እንደተቻለና ለዓለም ሀገራት ተምሳሌት መሆን እንደተቻለም አብራርተዋል።   ኢትዮጵያ ከውሃ አካላት እንክብካቤ፣ ከወንዞች ዳርቻ ልማትና ከሌሎችም ልማትና ዕድገት የሚያፋጥኑ ስራዎችን ሰው ተኮር ስራ በመስራት በከፍተኛ ፍጥነት የዕድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች ትገኛለችም ብለዋል። በመጨረሻም የቡድኑ ስብሰባ አዲስአበባ በመድረጉ በኢትዮጵያ ህዝብና በራሴ ስም ምስጋና እያቀረብኩ ክብር እንደሚሰማን መግለጽ እወዳለሁ ብለዋል።   በመድረኩ ሌሎችም የአፍሪካ ህብረትና የአህጉሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ንግግር አድርገዋል።

Share this Post