ድርቅን መቋቋም የሚችል ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት (CR wash) የስራ ነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ተካሄደ፡፡
የካቲት 26/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ድርቅን መቋቋም የሚችል ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት (climate resilient project) የስራ ላይ ነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ተካሄደ፡፡
በዕለቱ የግምገማ መድረኩን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ሲሆኑ ድርቅን መቋቋም ባለብዙ መንደር ፕሮጀክት (climate resilient project) የዋን ዋሽ(one Wash) አንድ ቋት ፕሮግራም አንዱ ዘርፍ ሲሆን 34 በመቶ ሽፋን ተሰጥቶት ወደስራ የተገባበት ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተው ከሁለት ወራት በፊት ውል ተፈርሞ በኦሮሚያ ክልል ወደስራ የገቡ ሶስት ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚቃኝ የግምገማ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ጋብዘዋል፡፡
በዚህ መሰረት በአማካሪዎቻቸው አማካኝነት የግምገማ ሪፖርታቸውን ያቀረቡት ፕሮጀክቶች የዳሮ ለቡ፣ዋጪሌና ኤልዋይ ሲሆኑ በሪፖርቱም በዋናነት የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ፊዚካል የስራ ሂደት፣የቁሳቁስ አቅርቦት፣የፋይናንስ ፍሰት፣በጥንካሬና በድክመት የተለዩ ጉዳዮችንና በሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና በመፍትሄነት ታሳቢ ቢደረግባቸው ያሏቸውን መሰረታዊ ነጥቦች በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ክቡር አምባሳደር በተጨማሪም በስራው ላይ ከተሰማሩት ኮንትራክተሮች፣በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክቱ ላይ ከሚሰሩ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ድጋፍና ክትትል ከሚያደርጉ አስተባባሪዎችና የፋናንስ ባለሙያዎች የትግበራ ሂደቱን አስመልከቶ ሃሳቦችና አስተያየቶችን እንዲያነሱ እድል በመስጠት ስራውን በጥልቀት ገምግመዋል፡፡
ከትራንስፖርት ጋር በተገናኘ የሚገጥሙ ተግዳሮቶች፣የቅድመ ክፍያ ሂደት እና ከነዳጅ እጥረት ጋር የተጠቀሱ ጉዳዮችም በክቡር አምባሳደሩ በኩል አስቸኳይ እልባት ተቀምጦላቸዋል፡፡
በተለይም የዳሎረቡ ፕሮጀክት ወደስራ ከተገባበት ጊዜ ገደብ አንስቶ በአንጻሩ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑና ዋጪሌ እና ኤልዋይ ደግሞ ውስንነቶች ስለሚታዩባቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲያጠናቅቁ በማድረግ ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች በበኩላቸው እስከ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም ድረስ አጠናቀው ርክክብ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም መደገፍ ባለበት መልኩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ክቡር አምባሳደሩ አሳስበዋል፡፡