ኢትዮጵያ በCop28 በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ቃል የተገቡ ጉዳዮችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗ ተገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በCop28 በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ቃል የተገቡ ጉዳዮችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗ ተገለጸ፡፡

ሚያዝያ 2016 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) እ.አ.አ. ከአፕሪል 21- 25/ 2024 ዓ.ም. በኔዘርላንድስ፤ ሮተርዳም ከተማ ‘’Redesigning Energy for people and planet’’ በሚል ርእስ በተካሄደው አለም አቀፍ የኢነርጂ ኮንግረስ ላይ የተሳተፉት የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስት ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በCop28 በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ቃል የተገቡ ጉዳዮችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ በተለይ ሁሉን አቀፍ የታዳሽ ሀይል ልማትና ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የታዳሽ ልማትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ እየተሰሩ ያሉትን ስራዎችንም አብራርተዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ኢትዮጵያ ወደ ታዳሽ ሀይል ልማት የሚደረገውን ሽግግር እንዲመጣ የበኩሏን አስተዋጾ እያደረገች መሆኗን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት የኢነርጂ ፖሊሲንና ስትረቴጂን በማሻሻል ይበልጥ የታዳሽ ሀይል ልማት ላይ ያተኮረ የኢነርጂ ልማት እንዲተገበር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢነርጂ ልማትና የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ የኢነርጂ ዘርፍ እቅድ አዘጋጅታ ወደ ስራ መግባቷን አንስተው፤ ይህም ኢትዮጵያ CoP28 በታዳሽ ሀይል ልማት ላይ የተደረሱትን ስምምነቶችን ለማሳካት እንደሚያስችላት ገልጸዋል፡፡

ዋና ዋና ኢነርጂ ተጠቃሚ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ኢነርጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል የፖሊሲና የስትራቴጂ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይ መንግስት የትራንስፖርት ዘርፉ የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ አስተዋጾ እንዲኖረው ለማድረግ የኤክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከታክስ ክፍያ ነጻ በማድረግና የተለያዩ ማበረታቻዎች በመንግስት በኩል እያቀረቡ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህም አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ከአለም አቀፍ ኢነርጂ ካውንስል ዋና ሀላፊ ከሆኑት ዶ/ር ማይህ ሀዋርድ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ኢነርጂ ካውንስል አባል መሆኗ ሊያስገኝ የሚያስችለውን ጥቅም ላይ ተወያይተዋል፡፡

Share this Post