በ ብራይት (BRIGHT) ፕሮጀክትን በኦሞ ጊቤ ቤዚን ለማስጀመር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በ ብራይት (BRIGHT) ፕሮጀክትን በኦሞ ጊቤ ቤዚን ለማስጀመር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ ጅማ፤ መጋቢት 12/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን የብራይት /Basin Management Support for Resilient, Inclusive Growth and Harmonized Transformation/ (BRIGHT) ፕሮጀክትን የኦሞ ጊቤ ቤዚን ለማስጀመር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡ መድረኩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ብራይት (BRIGHT) ፕሮጀክት በተመረጡት አምስቱ ቤዚኖች ላይ ማለትም አባይ፣ አዋሽ፣ ኦሞ-ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና የተከዜ ቤዚኖች ላይ የተሻለ የውሃ አጠቃቀምን ለማስፈን የቤዚን አስተዳደር ማስተባበሪያዎችን በማቋቋም ወደ ተግባር እየገባ ነው ብለዋል። በኔዘርላንድስ ኪንግደም ኤምባሲ (EKN)፣ በአውሮፓ ህብረት (EU)፣ በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል (WLRC) እና በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ የሚደገፈው ብራይት (BRIGHT) ፕሮጀክት ዘላቂ እና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን ለእርሻ፣ ኢንዱስትሪና ለቤት ውስጥ ፍላጎቶች በማዋል የውሃ አያያዝን ለማሻሻል ያለመ ነውም ብለዋል። በተፋሰስ ደረጃ የሚቋቋመው የኦሞ ጊቤ ቤዚን ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን (IWRM) የፕሮጀክቱን ግቦች ለማሳካት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ውይይቱ ኘሮጀክቱን በመደበኛነት በማስጀመር የፕሮጀክቱን አላማዎች፣ ግቦች፣ ወሰን እና የትግበራ ስትራቴጂ ላይ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር ነው ብለዋል። የኦሞ ጊቤን በቤዚን ደረጃ ለማስጀመር የኔዘርላንድ መንግስት እና የአውሮፖ ህብረት ለሚያደርጉት ድጋፍ አመስግነው የኦሞ ጊቤ ቤዚን ፕላንን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የሚመለከተው አካል የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል። በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የውሃ እና መሬት ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ የኦሞ ጊቤ ቤዚን ከፍተኛ የሀይድሮ ፓወር እና የብዝሀ ህይወት ያለበት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ባዮፊዚካልና ሶሺዮካልቸራል ሀብት ባለቤት የሆነውን ቤዚን በዘላቂነት ለመጠቀም የቤዚን አያያዝ ፕላን አዘጋጅቶ መተግበር ዋነኛ መንገድ ነው ብለዋል። ዶ/ር ጌቴ አክለውም የኦሞ ጊቤ ቤዚን ፅ/ቤት ለማቋቋም የመጀመሪያችን ቢሆንም የቤዚን ፕላን ትግበራው ያልተጀመረ በመሆኑ የቤዚኑ ማናጅመንት ፕላን ሊቃኝ ስለሚገባ የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል። በመድረኩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ እና በኢ/ያ የኔዘርላንድ ኢምባሲ ሴክሬታሪያት ሚ/ር የልመርን ጨምሮ ቤዚኑን ከሚጋሩ ክልሎች የኦሮሚያ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችና የሴክተር ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

Share this Post