የቶጎጫሌ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 97 ከመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ።
በ500 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቶጎ ጫሌ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፍና ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርገው ፕሮጀክትግንባታ 97 ከመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢ/ር ዶክተር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ፣ የሶማሌ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ ኢ/ር መሀመድ ሻሌን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮች ዛሬ የግንባታውን ሂደትና የሙከራ ስርጭት ተዟዙረው ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎችን ጨምሮ የሲቪልና የመስመር ዝርጋታ ስራ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን የገለፁት የፕሮጀክቱ መሀንዲስ ኢንጅነር አቤል ባዬ ለቀጣዩ 20 ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ የታቀደና በአንድ ግዜ ከሀያ አምስት ሺህ በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ማስጠቀም ያስችላል ብለዋል።
በተቀመጠለት የግዜ ገደብ ስኬታማ የሆነ ስራ መከናወኑን የጠቆሙት የፕሮጀክቱ መሀንዲስ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኖ ለምረቃ እንደሚበቃ ጠቁመዋል።
የውሃና ኢነርጂ አመራሮች የተሰራውን ስራ አድንቀው ከፕሮጀክቱ ጋ ተያያዥ የሆኑ የቦኖ ውሃ፣ የከብቶች ማጠጪያ ገንዳ፣ የጥበቃና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ የፕሮጀክቱ አካል የሆኑ ግንባታና የመስር ዝርጋታ ሂደቶችንም ተዟዙረው ተመልክተዋል።
የቶጎ ጫሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ ጥቅምት 19 / 2015 የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በጋራ ያስቀመጡት ሲሆን የፕሮጀክቱ ወጪም ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግስት በተለይም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንደሚሸፈን መገለፁ ይታወሳል።