ከ900 ኪሎ ዋት በላይ የሚያመነጩ አራት የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
ከ900 ኪሎ ዋት በላይ የሚያመነጩ አራት የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
ሀዊ ጉዲና:-ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሃዊ ጉዲና ወረዴ ከ900 ኪሎ ዋት በላይ የሚያመነጩ አራት የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ህብረተሰቡ የፀሃይ ኃይል ማመንጫዎችን እንደግል ንብረቱ እንዲጠብቅና የአገልግሎት ፍክያውን በወቅቱ መክፈል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በዓለም ባንክና በሌሎች አጋሮች በሚደገፈው ፕሮጀክት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ እና ብርሃን ተደራሽነት (ADELE) ፕሮግራም አማካኝነት የተተገበረ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቀረፁት 98 የገጠር ሶላር ሚኒ-ግሪዶች ውስጥ 38ቱ በኦሮሚያ ክልል የሚገነቡ ሲሆን፣ በምዕራብ ሐረርጌ ከተመደቡት 8 ፕሮጀክቶች መካከል 6ቱ አሁን ላይ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከሚኒግሪድ በተጨማሪ በተቋማት ኤሌክትሪፊኬሽን በሀገር አቀፍ 1ሺ 400 ተቋማትን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በዞኑ 32 የትምህርትና የጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ አስተማማኝና ጥራት ያለው አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በ2018 በጀት ዓመት በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዛሬ ከተመረቁት በተጨማሪ ሁለት ከተሞችን ከዋናው ግሪድ እንዲሁም ሁለት ቀበሌዎችን ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
ፕሮጀክቶቹ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ በሀዊ ጉዲና ወረዳ ባቴ፣ ቶርባን፣ ሃሮ ኦባ እና ሃሎ ጎባ ቀበሌዎች ላይ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡት ፕሮጀክቶች ከ900 ኪሎ ዋት በላይ የሚያመነጩ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ አባወራዎችን ጨምሮ የጤናና የትምህርት ተቋማትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ አቅም ሲኖራቸው፤ በአሁኑ ሰዓት ከ840 አባወራዎች ተጠቃሚ ያደርጋል።
በአራቱም ቀበሌ ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች 7.74 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር፣ 30.29 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እና 10 ትራንስፎርመሮች ተከላ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ ቶርበን 125 ኪ.ዋ፣ ባቴ 200 ኪ.ዋ፣ ሃሎ ጎባ 350 ኪ.ዋ እና ሃሮ ኦባ 225 ኪ.ዋ የማመንጨት አቅም አላቸው።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች፣ የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አመራሮች፣ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አመራሮች እና የሀዊ ጉዲና ወረዳ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ነዎሪዎች ተገኝተዋል።