ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኤሌክትሮመካኒካል ዕቃ አቅርቦትና ዝርጋታ ስራ የውል ስምምነት ተፈረመ።

ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኤሌክትሮመካኒካል ዕቃ አቅርቦትና ዝርጋታ ስራ የውል ስምምነት ተፈረመ። ሰኔ 20/2017 ዓ/ም ውኢሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒሰቴር ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሶማሌ ክልል፣ ኖጎብ ዞን እየተገነባ ላለው ለአዩን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የኤሌክትሮመካኒካል የዕቃ አቅርቦትና ዝርጋታ ስራ የውል ስምምነት ተፈራረመ። የውል ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲኔጋሞ የፕሮጀክቱ ሲቪል ግንባታ ስራው እየተፋጠነ እንደሆነ አንስተው የኤሌክትሮመካኒካል የዕቃ አቅርቦትና የዝርጋታ ስራውን ያሸነፈው ድርጅት ከዚህ ቀደም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በነበረው የስራ ውል ጥሩ አፈፃፀም እንደነበረው ገልፀው አሁንም የበለጠ አፈፃፀም በማሳየት በታቀደው ጊዜና ጥራት እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል ለፕሮጀክቱ ስራ ጥራትና ፍጥነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚያስፈልገው ሁሉ ኮንትራቱን ካሸነፈው ድርጅት ጎን እንደሚቆም አምባሳደሩ ገልፀዋል። የአግራባት የግንባታ እና ንግድ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አብርሃ ከሚስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር የመስራት ዕድል በድጋሚ በማግኘታቸው ደስ እንዳላቸው ገልፀው የተረከቡትን ስራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል። የፕሮጀክቱ ኤሌክትሮመካኒካል ዕቃ አቅርቦትና የዝርጋታ ስራው በ120 ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም በፊርማ ስነስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

Share this Post