የ88 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የግንባታና የቧንቧ ዝርጋታ የግዥ ሂደት ቅድመ ሁኔታ ላይ ከዘርፉ የግል ድርጅቶች ጋር ውይይት ተደረገ።
መጋቢት /2018 ዓ/ም ውኢሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፍሪካ ቀንድ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት የሚተገበር 88 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የሲቪልስራ ፣ የግንባታና የግዥ ሂደት ቅድመ ሁኔታ ላይ ከዘርፉ የግል ድርጅቶች ጋር በካፒታል ሆቴል ውይይት ተደረጓል።
የውይይት መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ሀብት አስተዳደር፣በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍና በኢነርጂው ዘርፍ ባለፉት 5 ዓመታት ሰፊ ስራ ተሰርቶ ፣በሶስቱም ዘርፍ በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በማብቃት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት የሚተገበሩ እንደ ሀገር በ55 ወረዳዎች 110 ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልፀው በዕለቱ የቀረበው የ88 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የሲቪል ስራ ፣የግንባታና የግዥ ሂደት ቅድመ ሁኔታ ውይይት ትልቅ ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በ2030 ለሁሉም ለዜጐቿ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እተሰራ ያለውን ስራ የሚያግዝ ከመሆን አልፎ በጎረቤት ሀገሮችም በኬንያ ፣በሶማሊያና በጅቡቲ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል ።
የዕለቱ ውይይት የሚያተኩረው በ88ቱ የመጠጥ ፕሮጀክቶች የሲቪል ስራና የቧንቧ ዝርጋታ የግዥ እና የጨረታ ሂደት ምን መምሰል እንዳለበትና ውጤታማ ስራ ለመስራት ቅንጅታዊ አሰራር ስለሚያስፈልግ የግል ድርጅት ተሳታፊዎች ቀናና ጠንካራ ሀሳብ በማዋጣት በውይይቱ እንዲሳተፉ አደራ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ስፔሻሊስትና የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት ቡድን መሪ አቶ አማኑኤል ተሾመ በበኩላቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች የፕሮጀከቶችን የግንባታ ሂደት የደረሰበትን በዝርዝር ይዘው እየተከተሉ መምራታቸው እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀው የግል ድርጅቶችም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት የግዥ አማካሪ አቶ ጃጋማ ቃበታ በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚካሄዱ የጨረታ ፣ የግዥ እና የኮንትራት ውል አሰጠጥ ሂደት ምን መምሰል እንዳለበት፣ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙና መፍትሄውንም ጭምር በሰነድ ለተሳታፊዎች አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የግዥ ከፍተኛ እስፔሻሊስት ኮማሮ ሪጆይስ/senior procurement specialist Komaro Rejoice/ አጠቃላይ የዓለም ባንክ ምን ዓይነት የግዥ ደንቦችንና መመሪያዎችን እንደሚከተል ምን ዓይነት ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥም እና በግዥ ህደት ሊደረግ ስለሚገባ ጥንቃቄ በሌሎችም በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሰነድ አቅርበው ተሳታፊዎች ተወያይተውበታል።
ከግል ድርጅቶች የመጡ ተሳታፊዎች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች ቁርጠኝነትና ከግል ድርጅቶች ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠንከር ስለሚያስፈልግ ሁላችንም የበኩላችንን በመወጣት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አለብን ብለዋል።