ከ82 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የተገነባው የመቆርቆር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ግንቦት 28/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነው በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ሙህር አክሊል ወረዳ የመቆርቆር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የወረዳው የዘመናት ጥያቄ የሆነው የመቆርቆር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን በሰፍራው ተገኝተው አብስረዋል።
ፕሮጀክቱን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ተገቢ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዞኑን የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ሊመልሱ የሚችሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን እንደሚገነባም ነው ክቡር አምባሳደሩ የገለጹት።
በቀጣይም ወቅየ እና ደንገዝ ቀበሌዎች ላይ የመጠጥ ውሃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ይቀመጣልም ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዞኑ የሚታየውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አየሠራ ላለው ስራ ፕሮጀክቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የወረዳው የሶስት ቀበሌዎች 13 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል።
ፕሮጀክቱ ለሌሎች አርአያ ሊሆን በሚችል መልኩ በህብረተሰቡ ተባባሪነት በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቅ መቻሉንም ገልጸዋል።
በቀጣይም ፕሮጀክቱን ወደ ክፍያ ስርዓት በማስገባት መጠበቅና መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ የምሁር አክሊል ወረዳ በዞኑ ውሃ አጠርና የውሃ ሽፋናቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ወረዳዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ችግሩን ተረድቶ ለዚህ በማብቃቱ ሊመሠገን ይገባዋል ብለዋል።
የውሃን ችግር መፍታት አጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መሠረት ነው ያሉት ሀላፊው ለችግሩ አንገብጋቢነት ሚኒስትቴር መስሪያ ቤቱ የሠጠው ምላሽ በእጅጉ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በስፍራው ተገኝተው የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር ተመልክተዋል።