ሰባት መቶ ሀምሳ ሺ (750,000) ቤተሰቦችን በሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሰባት መቶ ሀምሳ ሺ (750,000) ቤተሰቦችን በሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ነሃሴ 30/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክና የብርሃን ተደራሽነት ፕሮግራም (ADELE) በአለም ባንክ በሚደገፍ የ50.5 ሚሊየን ዶላር በጀት በቀጣይ አምስት ዓመታት ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ 750 ሺ አባውራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ፡፡

ፕሮግራሙ በአምስት ዓመታት ውስጥ ገጠራማ የሆኑና ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ከ2.5 አስከ 50 ኪሎሜትር ርቀው የሚገኙ አባውራዎችን የሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ ታላሚ ተደርጎ የሚተገበር ነውም ብለዋል፡፡

እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በፕሮግራሙ በሀገሪቱ 400 ወረዳዎች 350 ሺ አባውራዎችን የሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተበጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷልም ብለዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የመጀመሪያ ዙር የፕሮግራሙ አካል የሆነውን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ 45 ሺ በላይ አባውራዎችን በሰባት ክልሎች የሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለውንና 150 ሚሊየን ብር ወጭ የሚደረግበትን የውል ስምምነት ከዘጠኝ የሶላር ቴክኖሎጂ አቅራቢና አከፋፋይ አገር በቀል ድርጅቶች ጋር ተፈራርመዋል፡፡

በሶላር ሆም ሲስተም ቢያንስ ለአንድ ቤተሰብ አባላት ከአምስት (5) አስከ አስራ ሁለት (12) ዋት ፒክ ሀይል በማመንጨት ለመብራት፣ ለቻርጅ፣ ለሬዲዮና ለሌሎች መሰል አገልሎቶች ጥቅም ይሰጣልም ብለዋል፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ድርጅቶቹ በገቡት የውል ስምምነት መሰረት ጥራት ያለው ስራ በመስራት ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው በማሳሰብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርግላው አሳውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ውል የወሰዱ አገር በቀል ድርጅቶች ችግሩን በይበልጥ ተረድተው መንግስት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በሀይሉ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት አሻራቸውን ሲያኖሩ ወገኖቻቸውን እየጠቀሙ መሆኑን በመረዳት ለቀጣዩ ስራቸው ውጤታማነት ስንቅ የሚሆናቸውን መልካም ስራ በመስራት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲሉ ክቡር ሚኒስትሩ አቅጣጫና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

Share this Post