ከ611 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ አጠቃላይ ወጪ የመጠጥ ውሃ ግንባታና የውል አስተዳደር የማማከር ስራ የውል ስምምነት ተፈረመ።
ጥቅምት 27/2018 ዓ/ም ውኢሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በህዳጋሐሙስና በፍሬወይኒ ከ611 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ አጠቃላይ ወጪ የመጠጥ ውሃ ግንባታና የውል አስተዳደር የማማከር ስራ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
የውል ስምምነቱ የተፈረመው ከትግራይ የውሃ ጥናት፣ ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ የፍሬወይኒ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ19 ሚሊዬን ብር በላይ የግንባታውን የውል አስተዳደር ለማማከር እና ከትግራይ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር የህዳጋሐሙስን ከ279 ሚሊዬ ብር በላይ እና የፍሬወይኒ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ313 ሚሊዬን ብር በላይ የግንባታ ስራ ውል እንደሆነ ተገልጿል።
የውል ስምምነቱን የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ጨረታውን አሸንፈው የውል ስምምነቱን የፈረሙት ድርጅቶች ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ከዚህም በፊት የተለያዩ የማማከርና የግንባታ ስራዎችን በውጤታማነት ሰርተው ማስረከባቸውን አውስተው አሁንም የክልሉን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በፍጥነትና በጥራት በመስራት ከታቀደው ጊዜ ባጠረ ሁኔታ ሰርተው እንዲያስረክቡ አሳስበዋል።
ስራው እንዲቀላጠፍና ቅንጅታዊ አሰራር ጎልብቶ ስራው በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሆኖ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከከፍተኛ አመራር እስከ ባለሙያ ድረስ በሚያስ ፈልግ ሁሉ ከጎናችሁ ነን ብለው በቀጣይ የህዳጋሐሙስ ፕሮጀክት የውል አስተዳደር የማማከር ስራ ለመዋዋል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድርድር ላይ እንደሆነም ገልፀዋል።
ዶ/ር ኢ/ር መሓሪ ገ/ዮሐንስ የትግራይ ውሃ ጥናት፣ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ድርጅቱ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የትግራይንና የአጎራባች ክልሎችን ህብረተሰብ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው በውል የተረከቡትን የማማከር ስራ ከቀድሞ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እንደሚያከናውኑ ገልፀዋል።
ዶ/ር ኢ/ር መሓሪ አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትግራይ ክልልን ህብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚሰራው ስራ ባሻገር ሁለንተናዊ እገዛ እየደረገ መሆኑ ከዚህ ቀደም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የተመራ ልዑክ በክልሉ በመገኘት የተደረገው ጉብኝት ማሳያ በመሆኑ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል ።
ትግራይ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ በበኩላቸው የክልሉን የልማት ጥያቄ ከግምት በማስገባት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ያለው ስራ ለሌሎች የመንግስት ተቋማት መልካም ምሳሌ የሚሆን በመሆኑ በክልሉ ህዝብ ስም አመሰግናሐሁ ብለው የግንባታ ስራውን በባለቤትነት ስሜት በጥራትና በፍጥነት ሰርተን ለማስረከብ ቃል እገባለሁ ብለዋል።
ለፕሮገክቶቹ ግንባታ የሚፈጀው ጊዜ ለፍሬወይኒ ፕሮጀክት 15 ወራት ሲሆን ለህዳጋሐሙስ ፕሮጀክት 12 ወራት እንደሆናም ተገልጿል።