በ60 ሚልዮን ብር ወጪ የተገነባው የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
መጋቢት 29/2017ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር በምዕራብ ኦሞ ዞን ወኒት ሸሽ ወረዳ ይርኒ ቀበሌ በ60 ሚልዮን ብር ወጪ ያስገነባው የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በስፍራው ተገኝተው የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር ባበሰሩበት ወቅት በኢትዮጵያ መንግስት፣ ከዓለም ባንክ እና ከሌሎች የፋይናንስ ምንጭ የሚደገፈው የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም አካል በሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና መብራት ተደራሽነት/Access to distributed Electricity and Lighting in Ethiopia (ADELE) /ፕሮጀክት ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ እና ገጠራማ ለሆኑ ከተሞች ኤሌክትሪክ ተደራሽ ለማድረግ ፕሮግራም ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩልም ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 2 ነጥብ 5 ቢልዮን ብር 8ሜጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያላቸው እና 26 ሺ የገጠር ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 25 የሶላር ሚኒ ግሪዶች እየተገነቡ ሲሆን ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኛዎቹ በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንና የይርኒ ሶላር ሚኒ ግሪድ ኃይል ማመንጫም የዚሁ አካል መሆኑን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
100 ኪሎ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው የይርኒ ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት 5000 የአከባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በፕሮጀክቶች ፍትሃዊ የሆነ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት በመጀመሪያው ዙር ከሚገነቡት 100 ሶላር ሚኒ ግሪዶች ውስጥ ስምንቱ (በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገነቡ ሲሆን አሁን ላይ የግንባታ ዕቃዎች ወደ ሳይቶች የማጓጓዝ እና የሲቪል ስራዎች የተጀመሩብት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገርም በሶላር ሚኒ ግሪድ ሀይል ተደራሽ ለማድረግ ከተለዩት 400 በጣም ገጠራማ ወረዳዎች ውስጥ 19ኙ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ሲሆኑ፣ ስድስቱ(6) ደግሞ በምዕራብ ኦሞ ዞን ያሉ ወረዳዎች ናቸውም ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶች ዘላቂ አገልሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ይዞ መጠበቅና መንከባከብ እንዳለበት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አደራ ብለዋል፡፡
ምእራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንድሙ ደንባ በዞናችን ያሉ ወረዳዎች አብዛኞቹ የሚገኙት ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀው በመሆናቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው በአዴሌ ፕሮግራም የመብራት እድል ተጠቃሚ በመሆናችን ለይርኒ ቀበሌ ነዋሪዎች ትልቅ እድል ይዞ የመጣ ስለሆነ ለአስተባባሪዎቹ ምስጋና ይድረሳቸው ብለዋል፡፡ የይርኒ ቀበሌ ነዋሪዎችንም ለዘመናት ከነበሩበት ጨለማ በመላቀቃቸው እንኳን ደስአላችሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ ከለውጡ መንግስት ወዲህ ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ የገጠር የህብረተሰብ ክፍሎችን የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው የይርኒ ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክትም የመጋቢታውያን ፍሬ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ሊመሰገኑ ይገባልም ብለዋል፡፡