በልማት ስራዎች ጉብኝት፣ በ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና በተለያዩ ጉዳዮች ግንዛቤ በመፍጠር ሲካሄድ የነበረ መርሃግብር ዛሬ ተጠቃለለ።
ጥር 16/2018 ዓ/ም (ውኢሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በነቀምት ከተማና አካባቢ በተሰሩ በልማት ስራዎች ጉብኝት፣ በ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና ውይይት፣ በሪፎረም ስራና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ለተሳታፊዎች ግንዛቤ በመፍጠር ለ4 ተከታታይ ቀናት በነቀምት ከተማ ሲካሄድ የነበረ መርሃግብር ዛሬ ተጠቃሏል።
በማጠቃለያ መርሃግብር ለይ የውይይት መድረክ ሲመሩ የነበሩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የሁሉም ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ የ6ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት መቅረቡ አንዱ ክልል ከሌላው ክልል መልካምና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ልምድ በመለዋወጥ ሁሉም ወደተሻለ አፈፃፀም ደረጃ እንዲደርስ ስለሚያግዝ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተገበረ የሚገኘው 3ቱ የውሃ ሀብት ዘርፍ ፣የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ እና የኢነርጂ ዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው በእስትራቴጂክ ዕቅድ፣ በተሻሻሉ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና አዋጆች እና በተቋቋመው የተፋሰስ ምክር ቤት መመራትና መተግበር ስላለበት ጉዳዮች በከፍተኛ ጥንቃቄ የተዘገጁ ጥልቅና ሰፊ ሀሳብ የያዙ ሰነዶች ለተሳታፊዎች የቀረበበትን አግባብ ክቡር ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለው ሁሉም ፕሮጀክቶች እጅግ በጣም ብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የሚገነቡ በመሆኑ ተመርቆ ለአገልግሎት ከበቃ ጥቂት ወራት በኋላ አገልግሎቱ መቋረጥና የብልሽት ጥያቄዎች እንዳይነሱ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ፕሮጀክቶችን በትልቅ ጥንቃቄ መምራት አለብን ብለዋል።
በቀረቡት ሰነዶች ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ገንቢ ሀሳብ በማዋጣት የጋራ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ በሚያስችል መልኩ በውይይቱ እንዲሳተፉ ዶ/ር ሀብታሙ ተማጽነዋል።
የሪፎርሙ ትልቁ ዓላማ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ማሳለጥ በመሆኑ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ አተገባበሩና አፈፃፀሙ ወጥነት ያለውና ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ክቡር ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ከተለያዪ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመጡ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ከተፋሰስ አስተዳደር ከመጠጥ ውሃ አያያዝ፣ የታሪፍ አተማመንና የኢነርጂ አጠቃቀምን ከማዘመን አንፃር የተመዘገቡ የተሻሉ አሰራሮችንና ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶችና መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ለተሳታፊዎች አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ከኤሌክትሪክ ሀይልና ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የመጡ ተወካች በበኩላቸው እንደሀገር የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ ያለውን ስራ ፣በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ተግዳሮትና በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካል እንዴት በቅንጅት በመስራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ሀሳባቸውን በስፋት ለውይይት አቅርበዋል።
በማጠቃለያ ውይይት መድረክ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞች ከመጠጥ ውሃ፣ ከዘመናዊ መጸዳጃና ከዘመናዊ ኢነርጂ ተጠቃሚነት አንፃር ለምን በሁሉም ክልሎች ወጥና ተመሳሳይአይሆንም? ከኮንትራክተሮችና ከአማካሪዎች የአቅም ክፍተት ለመሙላት ምን እየተሰራ ነው? ከውሃ ፈንድና ከሌሎችም የብድር አመላለስ ክፍተትና በሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለተነሱ በሰፋፊ አስተያየቶችና በርካታ ጥያቄዎች ክቡር ሚኒስትሩና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የእስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ አለሙ መንገሻ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የነቀምት ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ስራስኪያጅ አቶ ገላና መኮንን በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአራት ቀናት የቆይታ መድረክ በነቀምት ከተማ እንዲሆን እድሉን ስለሰጠ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገሌፀው በራሳቸውና በአካባቢው መህበረሰብ ስም ልባዊ ምስጋናም አቅርበዋል።
የተለያዩ የመድረኩ ተሳታፊዎችም በነቀምት ከተማ በነበራቸው ቆይታ እና ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና እንክብካቤ ደስተኞች እንደነበሩ ገልፀው በቀጣይም የተለያዩ ሁነቶች በተለያዩ ክልሎች ቢዘጋጅ ጥሩ ነው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ትልልቅ ቁምነገሮችን፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ቁልፍ ስኬቶችን የ2015 በጀት ዓመትና፣ የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀምን ከ2017 በጀት ዓመት ጋር በንጽጽር በማሳየት አዝናኝና አስተማሪ ጉዳዮችንም ያካተተች የ2017 በጀት ዓመት አውታር ተብላ የተሰየመች ዓመታዊ መጽሔት ከብዙ ልፋት በኋላ ለንባብ መብቃቷን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ ስለመጽሔቱ ስራ ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት አብስረዋል።
የመጽሔቱ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ከመጽሔቱ ውስጥ አንኳር ጉዳዮችን የያዙ አጫጭር አንቀጾችን ለተሳታፊዎች በንባበብ አቅርበዋል ።
የመጽሔቱን ይፋዊ ምረቃ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና የአካባቢ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር አወቀ ሀምዛዬና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ ዶ/ር አረጋዊ በረሄ ገልፀዋል።