የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የሁለተኛው ምእራፍ የ6 ወራት አፈጻጸም እየተገመገመ ነው።
የካቲት 24/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የሁለተኛው ምእራፍ የስድስት ወር አፈጻጸም ላይ አወንታዊ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ።
በአፈጻጸም የግምገማ መድረኩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የሁለተኛው ምእራፍ ማጠናቀቂያ ላይ እንደመሆናችን የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በውጤታማነት በመፈጸም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ትልቁ ትኩረት ሰጥተን የምንተገብረው ነው ብለዋል።
የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም በተለያዩ ኮምፓነኔትች የሚተገበር ነው ያሉት ክቡር አምባሳደሩ በገጠር መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሀይጅን፣ በመካከለኛ ከተሞች የውሃ አቅርቦት ፣ ተቋማዊ የውሃ አቅርቦት፣ በሲአር ዋሽ እና ፕሮግራም አስተዳደር ላይ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቶቹ አተገባበር የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበ መሆኑን የገለጹት ክቡር አምባሳደሩ ፕሮጀክቶችቹ ተግባራዊ ሲደረጉ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ከመልካም አጋጣሚዎች ጋር በማስተሳሰር መተግበር መቻሉንም ነው የገለጹት።
በሁሉም ክልሎች ለታየው ጥሩ አፈጻጸም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ክልሎች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎችም ላደረጉት አስተዋጽኦ ክቡር አምባሳደሩ አመስግነዋል።
በቀሪ አስር ወራት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በሚገባ ለመፍታት ትልቅ ጥረት ማድረግ እንደሚገባና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ብሎም ያልተዘጉ ሂሳቦችን መዝጋት እና የመሳሰሉትን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው ክቡር አምባሳደሩ የጠቆሙት።
የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብይ ግርማ ከፌደራል ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ቡድን በየክልሎቹ በመዘዋወር በተደረገ የፕሮጀክቶቾ አፈጻጸም ምልከታ ሪፖርት መነሻነት ግምገማ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ግምገማው በሲአር ዋሽ የተከናወኑና በመካከለኛ ከተሞች በከፍተኛ ወጪ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም ድርቅን መቋቋም የሚችሉ 18 ፕሮጀክቶች ሁሉም ወደ ስራ የገቡና በቀሪ ወራት ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡ ነው የገለጹት።
በትምህርትና በጤና ተቋማት ላይም እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም አሳይተዋል ብለዋል።
የዋን ዋሽ ብሔራዊ ፕሮግራም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከጤና፣ ከትምህርትና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን ላይ ትኩረት አድርጎ በ308 ወረዳዎችና በ50 ከተሞች የጤናና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የሚተገበር መሆኑንም ነው አቶ አብይ የገለጹት።
ፕሮግራሙ በፈረንጆቹ 2027 የሚጠናቀቅ ሲሆን አጠቃላይ በጀቱም 589 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ ወደ ማጠናቀቂያ የደረሰ በመሆኑ የሚቀርቡ ሪፖርቶች የደረስንበትን ስለሚገልጹ በቀጣይ የምናሻሽለውንና አጠናክረን በተጀመረው አግባብ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የዛሬው የግምገማ መድረክ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ከፌደራል ተቋማት፣ ከአጋር የልማት ድርጅቶች፣ ከክልሎችና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በነገው እለትም እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።