ከ483 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የግንባታ ውል ስምምነት ተፈረመ።
ከ483 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የግንባታ ውል ስምምነት ተፈረመ።
ሀምሌ 01/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ጣንቋ አበርገሌ ወረዳ ከ483ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የብሄራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አካል በሆነው በCR-WaSH ፕሮጀክት የሚተገበር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከትግራይ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተር ፕራይዝ ጋር የግንባታ የውል ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ የሲቪል ስራ ግንባታ፣ የቧንቧ እና የመገጣጠሚያ ተከላ እና የኤሌክትሮ-ሜካኒካል እቃዎች አቅርቦት እና ተከላ የገጠር ቧንቧዎች የውሃ መስመር ዝርጋታን የሚያጠቃልል መሆኑ ተገልጿል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በተገባው የውል ስምምነት መሰረት በሚፈለገው የጥራት ደረጃና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ የህብረተሰቡ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲፈታ አሳስበዋል።
ክቡር አምባሳደሩ አያይዘውም በዋንዋሽ ናሽናል ሮግራም በሚተገበረው የባለብዙ መንደር ፕሮጀክት የሚኖሩት ማህበረሰቦች ለረጅም ጊዜ በውሃ እጥረትና በድርቅ የሚጠቁ አካባቢ በመሆኑ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ በክልሉ መንግስትና በክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ በኩልም የተለመደው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
የትግራይ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሙለታ ይርጋ ከዚህ በፊት በክልሉ ብዙ ስራዎችን የሰሩና አካባቢውን በቅርበት እንደሚያውቁት ገልጸው ስራውን በጥራትና ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀድመው እንደሚያጠናቅቁ ቃል ገብተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በ12 ወር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ 17 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡