ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የዳዬ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ግንቦት 11/2018(ው.ኢ.ሚ)የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሲዳማ ክልል ከ450 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የዳዬ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል!
በፕሮግራሙ የተገኙት የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ፕሮጀክቱ የሕዝብና የመንግሥት ቅንጅት ውጤት መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ሕብረተሰቡ ተገቢውን እንክብካቤ ሊያደርግለት ይገባል ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ፕሮጀክቱ የዳዬ ከተማ ሕዝብ የረጅም ጊዜ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ገልጸው ንፁህ ውሃ ማቅረብ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተቋሙን በጋራ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከ450 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና ከ75 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ከ88 ኪ.ሜ በላይ የመስመር ዝርጋታ፣ የ500 ሜ.ኪ ሪዘርቫየር፣ 12 የውሃ ቦኖዎች እና የአስተዳደር ሕንፃዎች ግንባታን ያካተተ ነው።
በምርቃት መርሀ ግብሩ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችና የዞኑ አመራሮች ታላቅ ደስታቸውን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።