ከ344 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ የባለ ብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ።

ከ344 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ የባለ ብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ። መጋቢት 06/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዋን ዋሽ ፕሮግራም ከ344 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ የአዩን የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል ኖጎብ ዞን፣ በአዩን ወረዳ የማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ። በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የሶማሌ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ከለውጡ ወዲህ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በውሃ፣ በጤናና በትምህርት የልማት መስኮች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል። ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የክልሉ መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው የውሃ ሽፋን ከክልል ክልል፤ ከአካባቢ አካባቢ ወጥነት እንደሌለው አንስተው፤ በተለይ ውሃ አጠርና ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎችን ታሳቢ በማድረግ የባለብዙ መንደር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ፕሮጀክት መተግበር መጀመሩንና የአዩን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል። አካባቢው ከፍተኛ የውሃ ችግር ስላለበት ፕሮጀክቱ ችግሩን ይፈታል ብለዋል። የአካባቢው የሐይማኖት አባቶች፣ ኡጋዞችና ወጣቶች ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በመርሃግብሩ ላይ የሶማሌ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ፤ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ፣ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል የብልጽግና ጽ/ቤት ሀላፊ ክቡር ኢ/ር መሀመድ ሻሌ፣ የክልሉ፣ የዞኑና የወረዳው የሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝቷል። በ21 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቀው ፕሮጀክት 37,000 የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። ፕሮጀክቱ በዋን ዋሽ ፕሮግራሞ የሲአርዋሽ (CR-WASH) አተገባበር አካል ሲሆን፤ የሲአርዋሽ (CR-WASH) 30 በመቶ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን ይታወቃል። የግንባታ ስራውን አሽኪር አጠቃላይየግንባታ እና የውሃ ስራዎች ኮንትራክተር ሲያከናውን የማማከር ስራውን የሶማሌ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ድርጅት ያካሂዳል።

Share this Post