በ340 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ለ12 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የጉድጓድ ቁፋሮ ውል ተፈረመ።

በ340 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ለ12 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የጉድጓድ ቁፋሮ ውል ተፈረመ።

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአማራ ክልል ለሚገኙ 12 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ በ340 ሚሊየን 288 ሺ 311 ብር ወጪ ከውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ጋር የውል ስምምነት ፈረመ።

ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ልማት ፕሮጀክት አካል ሲሆን፣ ተቋራጩ ተቋም የጉድጓድ ቁፋሮ እና ተያያዥ የውሃ ሥራዎችን በ60 ቀናት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ውል መውሰዱ ተገልጿል።

በውል ፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት፣ ውሃ የሕይወት መሠረት በመሆኑ መንግሥት ለንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።

“ይህ ፕሮጀክት በተለይ የውሃ እጥረት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች እፎይታ የሚፈጥር ነው” ያሉት አምባሳደሩ፣ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እና በተፈለገው የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቁ ተቋራጩ ከፍተኛ ሀላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን በበኩሉ፣ የተሰጠውን ሥራ በተፈለገው የጥራት ደረጃ እና በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር፣ በጤና፣ በንጽህና እና በኑሮ ሁኔታ መሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በWorld Bank ድጋፍ የሚተገበር መሆኑም ተገልጿል።

Share this Post