ከ34 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለ115 ከተሞች ተሰጠ።

ከ34 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለ115 ከተሞች ተሰጠ። ግንቦት 19/ 2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ በውሃ ልማት ፈንድ የሚተገብራቸው የድጋፍ ማዕቀፎች በአገሪቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻልና የሳኒቴሽን አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸው ተገለጸ። ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚተገብራቸው የድጋፍ ማዕቀፎች በሁለት ዋና አቅጣጫዎች የተደራጁ ሲሆን፣ አንደኛው “ቀጥታ ድጋፍ” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ የውሃ ፖሊሲ መሠረት “ወጪን በማስመለስ” መርህ ላይ የተመሠረተ የብድር ሥርዓት መሆኑን የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዶጊሶ ጎና ገልጸዋል። በቀጥታ ድጋፍ ማዕቀፍ ስር የሚሰጠው ድጋፍ በፌዴራል መንግስት፣ በልማት አጋሮችና በተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት የሚደገፍ ነው ያሉት መሪ ሰራ አስፈጻሚው በቀጥታ ለክልሎችና ለከተሞች በመተላለፍ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ ያግዛል ብለዋል ። ይህ ድጋፍ በተለይ ለገጠር መንደሮችና መለስተኛ ከተሞች አገልግሎታቸውን ለማስፋፋት ጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል። በሁለተኛው የድጋፍ ማዕቀፍ ስር ደግሞ ለመካከለኛና ትላልቅ ከተሞች ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ በብድር መልክ የሚያገኙ ሲሆን፣ ብድሩ በረጅም ጊዜ የሚከፈልና በአነስተኛ ወለድ የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው ይህም የውሃ ተቋማት በፋይናንስ ራሳቸውን እንዲችሉና ዘላቂ የአገልግሎት ሥርዓት እንዲፈጥሩ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል ። በውሃ ልማት ፈንድ ስር በሚተገበሩ ፕሮግራሞች አማካኝነት በ115 ከተሞች (133 ፕሮጀክቶች) ከ 34 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለመጥ ውሃ አቅርቦትና ለሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ባለፉት 15 ዓመታት የተሰጠ ሲሆን ይህ የፋይናንስ ድጋፍ አዳዲስ የውሃ መገኛ ቦታዎችን ለማልማት፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንኮችን ለመገንባት፣ የስርጭት መስመሮችን ለማስፋፋትና የፓምፕ ሥርዓቶችን ለማዘመን ወሳኝ ሚና መጫወቱን አቶ ዶጊሶ አክለው ገልጸዋል። እስካሁን ከተደገፉት 115 ከተሞች ( 133 ፕሮጀክቶች) ውስጥ በ97 ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን፣ ከ8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ንፁህና ዘላቂ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቶቹ በከተሞች ውስጥ የውሃ እጥረትን በመቀነስ፣ የህብረተሰቡን ጤና በማሻሻልና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማጠናከር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆነም ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው የገለጹት። በተጨማሪም ቀሪ 17 የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙና ሲጠናቀቁም ተጨማሪ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል። በሌላ በኩል “ባስኬት ፈንድ” በተባለው ፕሮጀክት 43 ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሲሆን፣ ይህ ፈንድ የተለያዩ የልማት አጋሮች (ከአውሮፓ ኢንቨስት መንት ባንክ ፣ ከጣሊያን እና ከፈረንሳይ ልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍን በአንድ ማዕቀፍ በማሰባሰብ እና ከክልሎች በሚዋጣ የፕሮጀክት መዋጮ ጋር በተቀናጀ መልኩ ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እንዲውል ማስቻሉን አክለው ነግረውናል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ከ88ሺ በላይ ዜጎችን ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርገውና ከ383 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሾኔ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ የውሃ መገኛ ልማት፣ የማጠራቀሚያ ታንኮች ግንባታ፣ የስርጭት መስመሮች ዝርጋታ እና የቧንቧ ትስስር ሥራዎችን በማካተት የተገነባ መሆኑንና ለከተማዋ ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በእጅጉ እንደሚያሻሽል መሪ ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

Share this Post