በ319,728,520.00 ብር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማልማትና ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
በ319,728,520.00 ብር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማልማትና ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.)
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋምቤላ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በ319,728,520.00 (ሦስት መቶ አስራ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሃያ ብር) የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማልማትና ስራ ላይ ለማዋል ከሁለት ኮንትራክተሮች ጋር ውል ተፈራረመ።
ፕሮግራሙ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሠ ምድር ውሃ የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮጀክት አካል መሆኑ ተገልጿል።
በጋምቤላ ክልል የሚካሄደው የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በሁለት ወረዳዎች የሚተገበርና በእያንዳንዱ ወረዳ አራት ጉድጓድ በጥቅሉ ስምንት ቁፋሮ የሚካሄድ ሲሆን ወጪው በድምሩ በ174,572,300 (አንድ መቶ ሰባ አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰባ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ብር ) ሲሆን ፋፊ የውሃ ስራዎች በተባለ ኮንትራክተር የሚገነቡ ናቸው።
እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ በአምስት ወረዳዎች የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማካሄድ በ145,156,220.00 ( አንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን አንድ መቶ ሀምሳ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ብር በሚደርስ ወጪ የሚሰራ ሲሆን ውል የተፈረመው ከፊያንዲሞ ትሬዲንግ ኃላ.የተ.የግል ኩባንያ ጋር ነው።
የውል ስምምነቱን የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ሲሆኑ ፕሮግራሙ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮጀክት አካል የሚተገበር መሆኑን አመልክተዋል።
ክቡር አምባሳደሩ በፊርማ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት እነዚህ ኮንትራክተሮች ቀደም ሲል በone WASH ፕሮግራም በነበሩ የፕሮጀክቱ ስራዎች ተወዳድረው በማሸነፍ በጥራትና በወቅቱ አስረክበው የነበረ መሆኑን አስታውሰው አሁንም ንጽህናውን የጠበቀ ውሃ ለማህበረሰቡ ለማድረስ በአጭር ጊዜና በጥራት አጠናቀው እንዲያስረክቡ አሳስበዋል።
ኮንትራክተሮቹ ቅድመ ሁኔታዎችን ህጋዊ በሆነ መንገድ አሟልተው ሲገኙ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም ክፍያዎችና ሌሎች ድጋፎች እንደሚደረጉላቸው ክቡር አምባሳደሩ አሳውቀዋል።
ኮንትራክተሮች በበኩላቸው ለተሰጣቸው ዕድል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱንም አመስግነው የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ፕሮጀክቶችን በወቅቱና በጥራት እንደሚያስረክቡ ቃል በመግባት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚያጋጥሙን ችግሮች ከጎናችን እንደሚቆም እንተማመናለን ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ተጀምረው እንዲጠናቁ የተያዘላቸው የጊዜ ገደብም ሦስት ወራት መሆኑ ተገልጿል።