ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የሆራ-አዘብ ከተማ የባለብዙ መንደር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
ሚያዚያ14/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ የሆራ-አዘብ የገጠር ከተማ እና የአካባቢውን ቀበሌዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የባለብዙ መንደር የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
በፕሮጀክቱ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድ ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን የውሃ ኢነርጂ ሚኒስቴር በአካባቢው ያለውን ችግር ተመልክቶ በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ በማድረግ ለአገልግሎት በማብቃቱና እውን እንዲሆን በማድረጉ አመስግነዋል።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በማከል ክልሉ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት እጦት የነበረበት ቢሆንም አሁን ላይ የተለያዩ ለውጦች መኖራቸው የሆራ-አዘብ የገጠር ከተማ እና የአካባቢው ቀበሌዎች መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡም ለፕሮጀክቱ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እስከተያዘለት የጊዜ ገደብ በሚገባ መጠቀም እንዲቻል በባለቤትነት እንዲጠብቁት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደተገነባ ገልጸው ፕሮጀክቱ የቢሮ ግንባታ ፣ የተሽከርካሪ እና ሌሎች ግብአቶች የተሟሉለት በመሆኑ ቀሪውን ስራ ክልሉ በማስተዳደር በተለይም የውሃ ክፍያ ስርዓትን በመዘርጋት ስራው እንዲቀጥል በማድረግ እና የአገልግሎት አሰጣጡን ፍትሃዊ በማድረግ የበኩልን እንዲወጣ እና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለክልሉ አደራ ሰጥተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ በማከል ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጾ ላደረጉ ለክልሉ ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ ፣ ለኮንትራክተሩ እንዲሁም ስራውን በቅርበት ሆነው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለተወጡ አካላትን በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ይህ የባለብዙ መንደር የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የኩርሙክ ወረዳ የሆራ-አዘብ የገጠር ከተማ ፣ እና የአካባቢውን ቀበሌዎች ከ15ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
የፕሮጀክት የግንባታ ስራው በዲኤንሲ (DNC) ኮንስትራክሽን ድርጅት የተከናወነ ሲሆን፤ ልህቀት የዲዛንና ሱፐርቪዥን ድርጅት የማማከር ስራውን ሰርቷል ፡፡