ለአዋሽ ተፋሰስ የውሃ መረጃ አንባቢዎች የ3 ቀናት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀመረ።

ለአዋሽ ተፋሰስ የውሃ መረጃ አንባቢዎች የ3 ቀናት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀመረ።

አዳማ፣ ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ)

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጸ ምድር ውሃ ዴስክ ለአዋሽ ተፋሰስ ጽ/ቤት የውሃ መረጃ አንባቢዎች በአዳማ ከተማ ድሬ ኢንተርናሽናል ቁጥር 2 ሆቴል የ3 ቀናት የአቅም ግንባታ ስልጠና ጀምሯል።

ስልጠናው በቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ከሚተገብራቸው አምስት ቁልፍ ተግባራት መካከል በተፋሰስ የሚሰበሰቡ የውሃ ሀብት መረጃዎችን በሥርዓት ማስቀመጥ፣ በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት እና የተቋማትን እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበትን የሚመለከተውን ቁልፍ ተግባር ለማሳካት ከሚከናወኑ ሥራዎች አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

በስልጠናው የላይኛው፣ የመካከለኛው እና የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ጽ/ቤቶች የውሃ መረጃ አንባቢዎች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ በሚቀርቡ የንድፈ ሐሳብና የተግባር ስልጠናዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉና ልምድ በመለዋወጥ ላይ ናቸው ።

የስልጠናው ዋና ዓላማ የውሃ መረጃ አንባቢዎች የውሃ ደረጃ፣ የዝናብ መጠንና ሌሎች የሀይድሮሎጂ መረጃዎችን በትክክል በመሰብሰብ፣ በተደነገገው ቅጽ በማስመዝገብ፣ በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት በማስተላለፍ እና የመለኪያ ጣቢያዎችን በአግባቡ በመጠበቅ ያላቸውን የሙያ ክህሎት ማሳደግ ነው።

በስልጠናው የሀይድሮሎጂ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች፣ የውሃ ከፍታ አንባቢዎች ሚናና ኃላፊነት፣ የውሃ ደረጃ አነባበብ፣ የመረጃ ምዝገባና ሪፖርት አቀራረብ፣ እንዲሁም የመለኪያ ጣቢያዎችን የአያያዝና የጥገና መርሆዎች በዝርዝር ተካተዋል።

ኢትዮጵያ 12 ተፋሰሶች ያሏት ሲሆን፣ በእነዚህ ተፋሰሶች የሚሰበሰበው የሀይድሮሎጂ መረጃ ለውሃ ሀብት ዕቅድ፣ ለጎርፍ ትንበያና ማስጠንቀቂያ፣ ለግድቦች አስተዳደር፣ ለመስኖ ልማት እና ለሌሎች የውሃ ሀብት አጠቃቀሞች መሠረታዊ ግብዓት በመሆኑ የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ለማልማትና ለማስተዳደር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።

Share this Post