በ25 ሚሊየን 732 ሺ 4 መቶ ብር በሚሆን ወጭ የክትትል፣ ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ውል ስምምነት ተፈረመ::

በ25 ሚሊየን 732 ሺ 4 መቶ ብር በሚሆን ወጭ የክትትል፣ ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ውል ስምምነት ተፈረመ፡፡ ሚያዚያ 1/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) አዲስ አበባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ25 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ የክትትል፣ ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዋን ዋሽ ፕሮግራም ሲአር ዋሽ ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነው በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከ32 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የጉራ ዳሞሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን የክትትል፣ ቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ስራ እንዲያከናዉኑ ከኢትዮጵያ ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን ጋር ውል ተወስዷል፡፡ የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የጉራዳሞሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሚፈለገው ደረጃ በጥራትና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተገንብቶ የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲፈታ የተደረገ የውል ስምምነት ነው ብለዋል፡፡ የውል ስምምነቱን የወሰደው የኢትዮጵያ ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ከአሁን በፊት ጥሩ ስራ የሰራና መልካም ግንኙነት ያለው ነው ያሉት ክቡር አምባሳደሩ የጉራዳሞሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትንም በሚፈለገው የቁጥጥር ደረጃ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ በታለመለት ጊዜና ጥራት እንደሚያከናውን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን ም/ስራ አስኪያጅ አቶ አዲስ እስማኤል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን እድል ስለሰጣቸው በማመስገን ከአሁን በፊት በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ያሳዩትን ጥሩ አፈጻጸም በመጠቀም ስራውን በጥራት፣ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

Share this Post