የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን እንዳስገኘላቸው ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን እንዳስገኘላቸው ተጠቃሚዎች ተናገሩ። የካቲት 12/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዴሌ ፕሮጀክት በሱማሌ ክልል በሶስት ዞኖች ስር በሚገኙ አራት ወረዳዎች ያስገነባቸው የሶላር ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየሰጡ ነው። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሙ ኒኬሽን ባለሙያዎችም በክልሉ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት በጀመሩት የሶላር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ከተጠቃሚዎቹ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የማህበረሰቡ ክፍሎች በከፍተኛ ሁኔታ መደስታቸውን አረጋግጠውላቸዋል ። በክልሉ በጀረር ዞን የዲግ ከተማ ነዋሪና በዲግ ጤና ጣቢያ በህክምናው ዘርፍ ከ8 ዓመት በላይ ያገለገሉት አቶ አብዱዋሂብ አሊ ከተማዋ ለረጅም ጊዜ የመብራት ተጠቃሚ አለመሆኗ በጤና ጣቢያው የሚሰጠው አገልግሎት ውጤታማና የህብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ እንዳይሆን እንቅፋት ሲፈጥርባቸው መቆየቱንና በተለይም በእናቶች የወሊድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሮባቸው እንደቆየ ገልጸዋል።   ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ከተማዋ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች በሚገባ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ በመሆናቸው አገልግሎታችን ጥራት ያለውና ተደራሽ እንዲሆን አስችሎናል ብለዋል። ከዚህ በፊትም በጀኔሬተር መበላሸትና በነዳጅ እጥረት ሰበብ ይከሰት የነበረው የተቆራረጠ አገልግሎት አሰጣጣችንን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እንድናከናውን በእጅጉ የሚያግዘን ትልቅ ስራን ለሰራልን ለፌደራል ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ ለፕሮጀክት አስተባባሪዎችና የዕድሉ ተጠቃሚ እንድንሆን ላስቻለን መንግስት ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል።   ፀጉር በማስተካከል የሙያ ዘርፍ ተሠማርቶ ያገኘነው ማርታዴ ድልነሳ በበኩሉ ከዚህ ቀደም በመብራት እጥረት ምክንያት በምሽት ብቻ እንዲሰራ ተገድቦ መቆየቱን አስታውሶ በዕለታዊ ገቢው በኩልም በተጠበቀው ልክ ውጤታማ እንዳልነበረ የገለጸልን ሲሆን አሁን በተገኘው እድል ደግሞ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ለመሰማራት መዘጋጀቱንና በዚህም ደስተኛ መሆኑን ገልጾልናል።   ሌላዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነችው ኒሞ እስማኤል የምስራቅ ጋሻሞ ከተማ ነዋሪ ስትሆን መብራት የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ በተለይ ደግሞ ሴቶች በቤት ውስጥ የምናከናውናቸውን ስራዎች በእጅጉ እያቀላጠፈልንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ለመሆን ስላስቻለን ለሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች እንኳን ደስ አለን ብላለች።

Share this Post