ከ202 ሺ ዪሮ በላይ በሆነ ወጪ የማማከር አገልግሎት የውል ስምምነት ተፈረመ።

ከ202 ሺ ዪሮ በላይ በሆነ ወጪ የማማከር አገልግሎት የውል ስምምነት ተፈረመ። ህዳር 09/2018 ዓ/ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሀገረ አሜሪካው አጎጊ ከሚባል አማካሪ ድርጅት ጋር ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ በ202,990. ዩሮ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በአቅም ግንባታ ፍላጎት፣ለክልሎች የአየር ንብረት ለውጥ የጥናትና ምርምር ስራ ፣ለአየር ንብረት ለውጥ መሻሻል የማሳያ ስራና ለዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ፍላጎት የማማከር አገልግሎት ለመስጠት የውል ስምምነት ተፈርሟል።   የውል ስምምነቱን ጨረታውን ካሸነፈው ድርጅት ጋር የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ኢትዮጵያ ዘመናዊ አሰራርንና መረጃ አያያዝን ተግባራዊ እያደረገች ባለበት በዚህ ወቅት ከአሜሪካው አጎጊ ድርጅት ጋር የስራ ውል መግባቱ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልፀው እድሉን ስላገኙ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ።   አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂም ይሁን በመረጃ አያያዝ ታዋቂ መሆኗን ያወሱት ሚኒስትር ድኤታው አማካሪ ድርጅቱ በዚህ አጋጣሚ በሀገራቸው ያለውን መልካም ተሞክሮዎች በሙሉ በማማከር ስራቸው ውስጥ በማካተት ለዘርፉ ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።   የአጎጊ አማካሪ ድርጅት ማኔጅንግ ዳይሬክተር ሚስተር ቲኦዶር ቲሃኒስ/Teodore Thehanis/ ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና እየገሰገሰች ባለችበት በዚህ ወቅት አብረን ለመስራት አጋጣሚውን በማግኘታችን ዕድለኞችነን ብለው ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣና በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ለማድረግ እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል ። የማማከር ስራው በውሉ መሠረት በጥራትና በፍጥነት በመስራት በ6 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

Share this Post