የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2018 ዓ/ም የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም በነቀምት ከተማ እየተገመገመ ነው።
ነቀምት # ጥር 14/2018 ዓ/ም ውኢሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2018 ዓ/ም የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም የግምገማና የውይይት መድረክ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና የአካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር አወቀ ሀምዛዬ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላትና፣ የሚኒስቴር የመስሪያ ቤቱ አመራሮች፣ የሁሉም ክልሎችና የ2ቱ ከተማ አስተዳደሮች የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊዎች፣ የዞኑና የነቀምት ከተማ አስተዳደር የመንግስት አመራሮችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ይፋዊ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በየበጀት ዓመቱ ሁለት ጊዜ በተለያዩ ክልሎች የሚደረገው የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና ውይይት መድረከ ውጤቶቻችንን ከፍ ለማድረግ ከማገዝ ባሻገር ባህሎቻችንንና መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ህብረብሔራዊ አንድነትንና ቅንጅታዊ አሰራርን ይፈጥራል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያከናውናቸው 3ቱ ዘርፎች የውሃ ሀብት አስተዳደር ፣ የኢነርጂ፣ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን ዘርፍ የሀገሪቱን ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም የያዘና ከፍተኛ ውጤትም እያሳየ መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ለመሠረታዊ ኑሮም ይሁን ለትልልቅ የሀገር ልማት መሠረቱ ውሃ ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለው ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት ከሚለው ትርክ ይልቅ የውሃ ሀብታችንን በመንከባከብ፣ በማጎልበት እና በማበልጸግ የህብረተሰባችንም ይሁን የጎረቤት ሀገራትን ፍትሀዊ የሆነ የጋራ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትን መረጋገጥ አለብን ብለዋል።
በውሃ አካላት ለይ ትኩረት ሰጥተን በመስራታችን ከውሃ ሀብት ከሚገኘው ጥቅም ባሻገር ዜጎችን ከጎርፍ አደጋ በመታደግ ውሃ ጥፋት መሆኑ ቀርቶ በረከት እንዲሆን ተደርጓልም ብለዋል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ አነሳሽነት የሚተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም ለገፀ-ምድርና ለከርሰ-ምድር የውሃ አካላት መበልፀግና መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አውስተው ሁሉም ባለድርሻ አካል አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ክቡር ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃት የሁሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የደም፣ የላብና የገንዘብ መስዋእትነት የተከፈለበትና የአንድነታችንና የጥንካሬያችን ማሳያ በመሆኑ ከተባበርንና ከተቀናጀን ዕቅዶቻችንን ማሳካት እንችላለን ብለዋል ክቡር ሚኒስትሩ።
በራሳቸው በክቡር ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት የዝናብ ውሃን በማጠራቀም የመጠቀም ዘዴ ለህብረተሰቡ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውና አዳዲስ ሀሳቦችን የማፍለቅና የመተግበር አቅም መኖሩንም ማሳያእንደሆነ ገልፀው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
የነቀምት ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ተመስገን ምሬሳ በበኩላቸው የብርቅዬና የቱባ በህሎች መገኛ፣ የንግድ ማዕከል፣ የታላላቅ ምሁራን መፍለቂያ ወደሆነችው ውቢቷ ነቀምት ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ነቀምትና አካባቢው ለሀገር ኢኮኖሚ፣ ለፖለቲካ ምህዳር መስፋት፣ ለመንፈሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደረገ አካባቢ መሆኑን አብራርተዋል።
በመርሃግብሩ የክልሎች የውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች የ6 ወራት ዋና ዋና የዕቅድ አፈፃፀም በሪፖርት ቀርቧል።
የግምገማና የውይይት መድረኩ በነገው ዕለት እንደሚቀጥልም ተገልጿል።