የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ገመገመ።

የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ገመገመ።

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) – በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የቤዚን አቀፍ የዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት (BaSRINET) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ለመገምገም ከፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የግምገማ መድረክ አካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ፣ በበጀት ዓመቱ የተመዘገበውን አፈጻጸም በጥልቀት መገምገም ጥንካሬዎችን ለማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን ለመለየትና ለማስተካከል እንዲሁም ለቀጣዩ በጀት ዓመት ግልጽ የሥራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በግምገማው የ2018 በጀት ዓመት ከዕቅድ አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን የሚያሳይ የአፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በዋናነት ትኩረት በሚያደርግባቸው የዋቢ ሸበሌና የአዋሽ ቤዚኖች የተመዘገበው አፈጻጸምም ውይይት ተካሂዶበታል።

በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) ድጋፍ የሚተገበረው ፕሮጀክት ዘመናዊ የውሃና የአየር ንብረት መረጃዎችን በቴክኖሎጂ ማደራጀት፣ ለሰዎችና ለእንስሳት ንጹህ የውሃ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የጎርፍ አደጋን መቀነስ፣ የአፈር መሸርሸርና የተፋሰስ ብክለትን ለመከላከል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወን፣ የባለሙያዎችን የቴክኒክ አቅም ማጎልበትና የታዳሽ ኃይል አማራጮችን ማስፋፋትን እንደ ቁልፍ ግቦቹ አስቀምጧል።

በግምገማው ወቅት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም፣ የፋይናንስና የፊዚካል ክንውኖች፣ የተስተዋሉ ውስንነቶችና መዘግየቶች በጥልቀት የተዳሰሱ ሲሆን፣ ከታዩ ክፍተቶች በመማር ለቀጣይ የመፍትሔ እርምጃዎች የሚወሰዱ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የተገኙ ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና የአፈጻጸም ማነቆዎችን በትብብር ለመፍታት ቁርጠኝነታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚያግዙ ገንቢ አስተያየቶችን አቅርበዋል።

በመድረኩ መጨረሻ በግምገማው የተለዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በወቅቱ በመፍታት የፕሮጀክቱን ውጤታማነት የበለጠ ለማሻሻል በቅንጅት እንዲሠሩ አጽንኦት ተሰጥቷል። በተጨማሪም የቀጣዩ በጀት ዓመት ረቂቅ ዕቅድ ቀርቦ በሚሰጡ አስተያየቶች መሠረት ተሻሽሎ እንደሚጸድቅ ተጠቁሟል።

Share this Post