የ2018ዓ.ም. የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አስፈጻሚ አካላት የስልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የ2018ዓ.ም. የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አስፈጻሚ አካላት የስልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡ ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም.(አዳማ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈጻሚ የ2018ዓ.ም. የግድቤን በደጄ የውሃ ማሰባሰብ ፕሮጀክት ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ለአስፈጻሚ አካላት የስልጠና መድረክ አመቻችቷል፡፡   በአዳማ ከተማ ፍላጎት ሆቴል እየተካሄደ በሚገኘው የስልጠና መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምሩ ገደፋ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ አነሳሽነት የተጀመረ ሲሆን ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በተለያየ መንገድ የሚገኘውን ውሃ በማሰባሰብ እጥረት በተከሰተ ወቅት ጥቅም ላይ የሚያውሉበት መንገድ ለማመቻቸት የተጀመረ መሆኑን ግብሩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አብራርተዋል፡፡   አቶ ታምሩ አክለውም ፕሮጀክቱ በመንግስት በሚሸፈን በጀት ተፈጻሚ እንደሚደረግና ቴክኖሎጂው ከጊዜ ቆይታ አንጻር ቆየት ያለ ቢሆንም የውሃ ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ በርካታ የተሻሻሉ ሁኔታዎች ታክለውበታል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ጅማሮ ጎንደርና ቦረና ላይ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን አቶ ታምሩ አስታውሰው በዚሁ ፕሮግራም በሃገራችን ውሃን ከዝናብ፣ከጎርፍ፣ከመሬት ውስጥ፣ከወንዝ እና ከጣራ ላይ በመሰብሰብ እስከ አሁን ድረስ በ219 ተቋማት ላይ በመገንባት ወደ የተለያዩ ክልሎች ተደራሽ በማድረግ በስፋት እየተሰራበት ነው ብለዋል፡፡   የአስቸኳይ ጊዜና ልዩ ድጋፍ ዴስክ ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት ተወልደ እንደገለጹት ደግሞ የዝናብ ውሃ ማሰባሰብ ፕሮጀክቱ በ2016 ዓ.ም ተጀምሮ ለተከታታይ አምስት ዓመታት የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የዝናብ ውሃ በማይገኝባቸው የጤና፣የትምህርት እና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ውሃ ለማዳረስ እንዲቻል ቀደም ሲል የተዘጋጀውን ዲዛይን በማሻሻል በስራው ለሚሳተፉ አካላት በማስተዋወቅ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን መንገድ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንዲቻል ስልጠናው እንዲካሄድ መደረጉን አልክተዋል፡፡   የስልጠና ሰነዱ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈጻሚ የአስቸኳይ ጊዜና ልዩ ድጋፍ ዴስክ ከውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ጋር በጋራ የቀረበ ሲሆን የዓለም የውሃ ሃብት መረጃ፣የጣሪያ ዝናብ ውሃ ማቆር ታሪካዊ አጀማመር፣በትግራ ሂደት ነበሩ ተግዳሮቶችና የተቀየሩ ዲዛይኖች፣እስከአሁን ድረስ የመጡ ለውጦች፣እንዲሁም ከአፍሪካ እና ከዓለም ሃገራት የተገኙ ተሞክሮዎች ተካተውበታል፡፡   በስልጠናው ላይ የክልሎችና የወረዳ ውሃ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ሃላፊዎች እንዲሁም ስራ ተቋራጮች መድረኩ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ ላይ መገኘታቸው ቀደም ሲል የነበራቸውን ግንዛቤ እንዳሰፋላቸውና ለቀጣይ ስራዎች የሚገጥሙ ችግሮችን እንደሚፈታላቸው አስረድተዋል፡፡ የስልጠና መድረኩ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በርካታ ሃሳቦችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች የሚሰነዘሩና የሚዳብሩበት እንደሆነ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

Share this Post