የብሄራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 እቅድ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ።

የብሄራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 እቅድ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ። ሚያዚያ 30/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ ) የብሄራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 እቅድ መመሪያ ላይ በሐዋሳ ውይይት እየተካሄደ ነው። በአፈፃፀም ግምገማው ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ፕሮግራሙ በሁሉም ክልሎችና በአራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አምስት ማእቀፎችን አቀናጀቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልፀው በዘጠኝ ወሩ የፕሮግራሙ ትግበራ የተከናወኑ ተግባራት የፋይናንስና ኮንትራት አስተዳደር፣ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማን ጨምሮ በትኩረት የተሰሩ ስራዎችን አብራርተዋል። በዘርፉ ለህዝባችን መስራት ያለብንን የልማት ስራዎች በሚገባ በመገንዘብ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በቀጣይ የተለየና ምዘናን መሰረት ያደረገ ባህሪ እንደሚኖረው የዓለም ባንክን የመመዘኛ መስፈርት መሰረት አድርጎ መስራትና የፋይናንስ አጠቃቀምን በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ፣ ወቅቱንና አሰራሩን የጠበቀ የሂሳብ ሪፖርት ማቅረብ እንደሚገባም ክቡር ሚኒስት ዲኤታው አሳስበዋል። የሲዳማ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ኢ/ር ከበደ ገኖሌ የዋን ዋሽ ፕሮግራም በውሃው ሴክተር ትልቅ ለውጥ ያመጣ ፕሮግራም መሆኑን ጠቁመው አሁንም አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያላገኘ በመሆኑ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በጥልቀት በመገማገም አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የብሄራዊ ዋን ዋሽና ሳኒቴሽን ፕሮግራም እንደ ክልል የከተማና የገጠር መጠጥ ውሃ ሽፋን ከመቶ ሺ በላይ ተጠቃሚ ብናደርግም ፍሳሽ አወጋገድ ላይ ብዙ ለውጥ ያልታየበት ስለሆነ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባልም ብለዋል፡፡ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር ባቀረቡት የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፓርት ላይ በመነሳት የብሔራዊ ዋን ዋሽ አስተባባሪ አቶ አብይ ግርማ ማጠቃለያ ሰጥተዋል። በቀረቡት ሪፓርቶች ላይ ለተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በመጨረሻም የ2018ዓ.ም በጀት አመት የእቅድ መመሪያ ዙሪያ ውይይቱ የሚቀጥል ሲሆን የሁሉም ክልሎች ተወካዮች እና የሚመለከታቸው አካላት በውይይቱ እየተሳተፉ ነው።

Share this Post