የብሔራዊ የአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ኃይጂን ፕሮግራም የ2015 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም እና የ2016 ዓ.ም እቅድ የስትሪንግ ኮሚቴ ገምግሞ አፀደቀ።
ነሐሴ 17, 2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ብሔራዊ የአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ የሳኒቴሽንና የኃይጂን ፕሮግራም እቅድ አፈጻጸም በአራቱ የዋሽ አስፈፃሚ አካላት ( የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች) እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የፕሮግራሙ ምዕራፍ ሁለት ያለበትን ደረጃ የስትሪንግ ኮሚቴው በካፒታል ሆቴል ገምግሟል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ፋንታ ማንዳፍሮ እና የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በተገኙበት በተካሄደው ውይይት፤ የመጠጥ ውሃ የሳኒቴሽና የሃይጂን ሽፋንን ለማሳደግ በሁሉም ክልሎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሥራት እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
የ2015 ዓ.ም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የሳኒቴሽን አገልግሎት ፕሮጀክቶች እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ኃይጂን ፕሮግራም ማስተባበሪያ ሃላፊ አቶ አብይ ግርማ የቀረበ ሲሆን የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ቀርቦ ውይይት ተካሂደዋል።
ከፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ከባለድርሻ አካላት በኩል ለተነሱት ጥያቄዎች በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ተሰጥተዋል ። ክቡር ሚኒስትር ድኤታው አያይዘው የተቋማት ሪፎርም፣ የፀጥታ ሁኔታ፣ የግንባታ እቃዎች ዋጋ ንሰትና የግዥ ሂደት መጓተት በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ብለዋል ።
የ2016 ዓ.ም እቅድ ለክልሎች 7 ቢሊየን እና ለፌደራል 5.2 ቢሊየን በድምሩ ከ12.24 ቢሊየን ብር በላይ ለመጠጥ ውሃ፣ ለሳኒቴሽንና ለኃይጂን ሥራ እንቅስቃሴዎች በሁሉም የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የገንዘብ ተቋማት ለመተግበር ስትሪንግ ኮሚቴው አፅድቋል።