ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገዙ 13 ኮምፒዩተሮችን ለከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፅ/ቤቶች ድጋፍ ተደረገ።

ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገዙ 13 ኮምፒዩተሮችን ለከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፅ/ቤቶች ድጋፍ ተደረገ።

የካቲት /2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገዙ 13 ኮምፒዩተሮችን ለ13 ከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፅ/ቤቶች ድጋፍ አደረገ።

በርክክቡ ወቅት የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ድጋፉ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የውሃ አገልግሎት ተቋማትን አቅም ለማጎልበት ከሚያደርገው ድጋፍ አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ የውሃ አገልግሎት ስራውን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚቀጥልና በቀጣይ የህዝቡን የውሃ ችግር ለመፍታት በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዶጊሶ ጎና በውሃ ልማት ፈንድ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በየክልሉ ካሉ ድርጅቶች ጋር ስለሚሰራ፤ በበጀት አመቱ ከተቋሙ ብድር ወስደው ህብረተሰቡን ውሃ እያጠጡ ያሉትን ከ108 ከተሞች ውስጥ ለተወሰኑት የአቅም ግንባታ ስራ ለመስራት በተያዘው እቅድ መሰረት ተግባራዊ መደረጉን ገልፀዋል።

አቶ ዶጊሶ አያይዘውም ከዚህ በፊት የሞተርሳይክል ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰው፤ በዛሬው እለትም ለኦሮሚያ፣ ለአፋር፣ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራና ሱማሌ ክልል 13 ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮችን ከነፕሪንተሩ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ከሚኒስቴር መስሪያቤታችን ጋር በጋራ የሚሰሩ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ የጣልያን ልማት ድርጅትና የፈረንሳይ የልማት ድርጅት በተገኘ ድጋፍ አማካኝነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮምፒዩተሮቹን የ13ቱ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፅ/ቤት ተወካዮች ከክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ተረክበዋል።

Share this Post