በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ዙሪያ የከርሰ ምድር ውሀ ሀብት አለኝታ ልየታና ልማት የሚውል የ11 የጉድጓድ ቁፋሮ ውል ተፈረመ
ህዳር 02/2018 ዓ.ም (መውኢ) በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ዙሪያ በ538 ሚሊየን 262 ሺህ 866 ብር ወጪ የከርሰ ምድር ውሀ ሀብት አለኝታ ልየታና ልማት የሚውል የ11 የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ሊካሄድ ነው፡፡
ከርሰ ምድር ውሀ ሀብት አለኝታ ልየታና ልማት የሚውል የ11 የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ፕሮጀክቱን ለማከናወን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር የውል ስምምነት ፈጽሟል።
የውል ስምምነቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ እና የውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራስኪያጅ አቶ አስናቀ እንዳለማው ተፈራርመዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ሥራው የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ በተቀመጠለት ውል መሰረት መጠናቀቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አክለውም ክቡር ሚኒስትሩ በተለያዩ ምክንያቶች መጓተት ካለ ለማህበረሰቡም ለኮንትራክተሩም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው በማስገንዘብ፤ ችግሮች ካጋጠሙ በወቅቱ በመናበብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲሚድረግ አረጋግጠዋል።
የውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ወክለው የተፈራረሙት የኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ እንዳለማው በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱን በ538 ሚሊየን 262 ሺህ 866 ብር በጥራት ያከናውናል ብለዋል።
ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቀረበለት የኮንትራት ውል መሰረት በተቀመጠው የቴክኒክ ዝርዝር በጊዜ ገደቡ የውል ግዴታውን አሟልቶ እንደሚፈጽም ገልጸዋል።
ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ያለውን ዝግጁነት በማረጋገጥ የውል ስምምነቱን በመፈረም ኮርፖሬሽኑ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እምነት ተጥሎበት ፕሮጀክቱን ለመፈጸም ውል እንዲገባ በመደረጉም ምስጋና አቅርቧል። ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ 210 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ (grant ) አካል ሲሆን ዛሬ የተፈረመው ቁፋሮው በ538 ሚለዮን 262 ሺህ 866 ብር በሞጣ መካነ ሠላም ዙሪያ የሚከናወን ሆኖ በውሉ መሠረት በ240 ቀናት እንደሚጠናቀቅ ተገልፆል።
በፊርማው ሥነ ሥርዓት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ተገኝተዋል፡፡