ከ11 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ የተገነባው የአቅመ ደካሞች ቤት ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ተሰጠ።
ሰኔ 20/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የተመራው ቡድን በጋምቤላ ክልል በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ከ11 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነቡ ቤቶችን ለ5 አቅመ ደካሞች አስተላልፈዋል።
በእለቱ የጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶ/ር ጋትልዋክ ሪዮን በጋምቤላ ከተማ አምስት ቀበሌዎች ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያስገነባቸው የአቅመ ደካሞች ቤት ርክክብ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በክልላቸው በተለያዩ በጎ አድራጊዎች ከ57 በላይ ቤቶች መገንባታቸው የመተባበር ፣ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ11ሚሊየን ብር በላይበሆነ ወጪ ካስገነባው ቤት በተጨማሪ በክልሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን እየሰራ ያለ በመሆኑ በክልሉ ህዝብ እና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በጎንደር ከተማ የተመጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል በተለያዩ አካባቢዎች የአቅመደካማ ቤቶችን እያስገነባ እያስተላለፈ ይገኛል ብለዋል።
በጋምቤላ ከተማ ላደረግነው ድጋፍም ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስካሁን ከ30ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የበጎ ፈቃድ ስራ እየሰራ እንዳለ የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተያዘው ክረምትም በአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች በ3 ወረዳዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የቤት ድጋፍ የተደረገላቸው ወ/ሮ አካንጎ ኡዲየል ቻሞ እስካሁን ጸሀይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ሲቸገሩ የቆዩ መሆኑን ገልጸው መንግስት ስላደረገላቸው ድጋፍ በእጅጉ አመስግነዋል ።
እሳቸው ያገኙትን እድል ሌሎችም እንዲያገኙ ያላቸውን ምኞች ገልጸዋል።
ቤቶቹን ባይጌታ ኮንስትራክሽን በአጭር ጊዜ በጥራት ገንብቶ በማጠናቀቁም ሊመሠገን እንደሚገባ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
በርክክብ ፕሮግራሙ የጋምቤላ ክልል ከንቲባ፣የምክር ቤት አባላት ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ባለሙያዎችእና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።