በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ 100 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ 100 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለምአቀፍ ሶላር አልያንስ (ISA) ጋር በመተባበር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ የተገነባ 100 ኪሎ ዋት የሚያመነጭና የሀይል አቅርቦትን የሚሸፍን የሶላር ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ተቋሙ በሶስት ዘርፎች ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በኢነርጂው ዘርፍ እንደሀገር 6.8 ጊ.ዋ ተደራሽ ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡ ከሶላር ኢነርጂ 10 ሺ የሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መደረጋቸውን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ አባል በመሆኗ በሶላር ሰርቶ ማሳያ እንዲሆን የተገነባውና አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሶላር ፕሮጀክት ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚገባ ነው ብለዋል። የሶላር ፕሮጀክቱ በመጠጥ ውሃ፣ በኢነርጂና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋትም ያግዛል ብለዋል ክቡር ሚኒስትሩ፡፡ በቀጣይ የክትትል ስርዓት በመዘርጋት ፤ ማኑዋሎችንም ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበው ፕሮጀክቱን ለደገፈው አለማቀፍ ሶላር አሊያንስና በስራው ሂደት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ፕሮጀክቱ 200 ሺ ዶላር ወጪ የተደረገበትና የተመረተው ኃይል ቀጥታ ወደ ግሪድ የሚገባ አሰራሩ ፍጆታን በብቃት ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ተገልጿል።

Share this Post