እ.ኤ.አ ከሜይ 1 እስከ 10/2024 የሚኖረው የአየር ሁኔታ
እ.ኤ.አ ከሜይ 1 እስከ 10/2024 የሚኖረው የአየር ሁኔታ
///////////
በሜይ የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ስፍራዎች ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚኖራቸውና በተለይም የምድር ወገብን አቋርጦ ወደ ሀገራችን የሚገባው ዕርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተሻለ የደመናና የዝናብ ሥርጭት በደቡባዊው አጋማሽ፤ በመካከለኛው እና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ፤ በደቡብ ምስራቅ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ፣ በመካከለኛው፣ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡
በተጨማሪም በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ መካከለኛው፤ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቅጸበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፤ ቦረና፤ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፤ አዲስ አበባ፤ ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የዋግህምራ፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የአፋር ክልል ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፤ የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሱማሌ ክልል ዞኖች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፤ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ፣ ሁሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር፤ ከአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ ፣የምስራቅና የምዕራብ ጎጃም ዞኖች፤ የጋምቤላ ክልል ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ክልል የአሶሳ፣ የማአኮሞ ልዩ ወረዳ፤ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ። በተጨማሪም በአፋር ክልል፤ ሀረር፤ ድሬዳዎ፤ የሶማሌ ክልል ዞኖች፤ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በምስራቅ አማራ አካባቢዎች ከሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በመነሳት ቅጸበታዊ ጎርፍ የማስከተል አቅም ስለሚኖረው ከወዲሁ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያሳስባል።