የዘመናት የመብራት ጥያቄያችን ምላሽ አገኘ ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ
የዘመናት የመብራት ጥያቄያችን ምላሽ አገኘ ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ
ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዙሪያ የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የዘመናት የመብራት ጥያቄያቸውን የመለሱላቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ።
በኦሮሚያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ከድር ሁሴን፣ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችና አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት መግባቱ ለዓመታት የቆየውን የሕዝብ ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሕይወት የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የአካባቢዎቹን የልማት ዕድገት ለማፋጠን አስተዋፅዖ እንደሚያደርግም አክለዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሀመዲን ከቢር ሁሴን በበኩላቸው፣ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶቹ በቀበሌዎቹ አነስተኛ ንግዶች እንዲስፋፉና የገቢ ምንጮች በመፍጠር አዲስ አቅም እንደሚፈጥሩ ገልፀዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች ስልክ ለመሙላትና የወፍጮ አገልግሎት ለማግኘት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ሲጓዙ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መሀመዲን አሁን ግን በየቤቱ የኤሌክትሪክ ብርሃን ማግኘታቸው የነዋሪዎችን ጫና እንዳቃለለ ተናግረዋል።
የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሠራተኛ አቶ መኮንን ፍቅሬ ቀደም ሲል በአካባቢው የተነሳው የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ እንዳገኘ ጠቅሰው፤ አሁንም የዘመናት የመብራት ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከአስር ዓመታት በላይ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አለምፀሐይ በፍቃዱ፣ ልጆቻቸው በቂ ብርሃን አግኝተው ትምህርታቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲከታተሉ መቻላቸውን ገልፀው፤ ከኩራዝ የሚወጣው ጭስና ለማገዶ እንጨት ለመልቀም የሚያጠፉት ጊዜና ድካም እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ ታቶ አለማየሁ በበኩላቸው፣ የኤሌክትሪክ አለመኖር በትምህርትና በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥርባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን በኤሌክትሪክ ምግብ ማብሰል፣ እንጀራ መጋገርና ቡና ማፍላት በመቻላቸው የቤተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ማቃለሉን ተናግረዋል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto