በተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ዙሪያ የተካሄደው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ገንቢ ሀሳቦችን አስገኘ።
በተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ዙሪያ የተካሄደው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ገንቢ ሀሳቦችን አስገኘ።
ሀምሌ 20/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.)
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው በተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ዙሪያ የተካሄደው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በፌደራልና በክልል ተቋማት፣ በዘርፉ ባለሙያዎችና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ተካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በረቂቅ ደንቡ ላይ ገንቢ አስተያየቶችን በማቅረብ፣ የተፋሰስ ምክር ቤቶች በህጋዊ ማዕቀፍ መደራጀታቸው ለተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ለዘላቂ የተፋሰስ አስተዳደር፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለሀገራዊ ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ በተለይም የህብረተሰቡ ተሳትፎ በሁሉም የውሳኔ ሂደቶች እንዲጠናከር፣ ለደንቡ አፈጻጸም የሚያግዝ ቴክኒካል ኮሚቴ እንዲቋቋም፣ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በተፋሰስ ልማት የላቀ ሚና እንዲኖራቸው እንዲሁም የአቅም ግንባታ፣ የግንዛቤ ፈጠራ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች እንዲጠናከሩ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተጨማሪም በተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት እንዲጠናከር ጥሪ ቀርቧል።
በውይይቱ ወቅት የረቂቅ ደንቡ የተለያዩ አንቀጾች ላይ ዝርዝር ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ የሴክተሮች ቅንጅትና ትስስር በበለጠ ግልጽነት እንዲቀመጥ፣ የቤዚን ጽሕፈት ቤቶች ሚናና ኃላፊነት በግልጽ እንዲገለጽ፣ የውሃ ሀብት ጥበቃና ልማትን የሚደግፉ ድንጋጌዎች እንዲጠናከሩ እንዲሁም በተፋሰሶች ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በህጋዊ ማዕቀፍ የሚፈቱ አሠራሮች እንዲካተቱ ጥቆማዎች ቀርበዋል።
ለተነሱት ሀሳቦች ምላሽ በሰጡት የመድረኩ መሪዎች፣ ሁሉም ገንቢ አስተያየቶች ከህጋዊ ማዕቀፉ ጋር በማጣጣም በጥልቀት እንደሚመረመሩና ተገቢው ማሻሻያ ተደርጎ በመጨረሻው ረቂቅ ደንብ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።
ውይይቱን በማጠቃለል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት፣ በመድረኩ የቀረቡት ገንቢና ጠቃሚ አስተያየቶች የታቀደውን ዓላማ ያሳኩ መሆናቸውን ገልጸው፣ አስተያየቶቹ በረቂቅ ደንቡ ውስጥ በሚገባ ተካተው የበለጠ የተሟላና ውጤታማ የህግ ማዕቀፍ እንዲሆን እንደሚያስችሉ አስታውቀዋል።
እንዲሁም ለደንቡ ስኬታማ ትግበራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሰጡትን ድጋፍ በተግባር በመተርጎም ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።